Fana: At a Speed of Life!

የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር መተላለፊያ የማግኘት መብታቸው ሊከበር ይገባል – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ያልተቋረጠ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር መተላለፊያ የማግኘት መብታቸው ሊከበር ይገባል አሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ።

ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ኮንፍረንስ በተርኪሚኒስታን እየተካሄደ ይገኛል።

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በኮንፍረንሱ ባደረጉት ንግግር÷ የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ቀጥተኛ የባህር በር መተላለፊያ አለማግኘት፣ከፍተኛ የትራስፖርት ወጪ እና መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላትን ጨምሮ በሌሎች መሰረታዊ ችግሮች እየተፈተኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡።

የጂኦ ፖለቲካ ውጥረቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ከፍተኛ የእዳ ጫና ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ ምክንያት መሆናቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የመሬትን 50 በመቶ እና የዓለምን 60 በመቶ የውቅያኖስ ስፍራ የሚሸፍኑት ዓለም አቀፍ የውሃ ሀብቶች የሁሉንም ሀገራት ብልጽግና የማረጋገጥ ትልም እንደሚያሳኩ በጽኑ ታምናለች ብለዋል።

የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ያልተቋረጠ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር በር መተላለፊያ የማግኘት መብታቸው ሊከበር እንደሚገባም ነው ሚኒስትሩ አጽንኦት የሰጡት።

ይህም ከትራንዚት ባለፈ የሀገራት ሁሉን አቀፍ መብት መሆኑን በውል መረዳት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው÷ የሀገራቱ ፍላጎት በማሪታይም የኢኮኖሚ እድሎች ተጠቃሚ መሆን፣የአካባቢ ጥበቃ እና የማሪታይም ደህንነት መጠበቅ ጭምር እንደሆነም አንስተዋል።

የባህር በር መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦች ሙሉ ለሙሉ ሊተገበሩ እንደሚገባ የጠቀሱት ሚኒስትሩ÷ ይህም ዘላቂ እና የጋራ ልማትን ለማምጣትና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ቁልፍ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ኮንፍረንስ የባህር በር ማግኘት ላይ የእይታ ለውጥና ዓለም ለጉዳዩ ያለው ቁርጠኝነት ዳግም ይታደስበታል ብላ እንደምትጠብቅ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሀብት ማሰባሰብ እና አዳዲስ የመፍትሄ ሀሳቦች የሚያመጡ ውጤታማ ትብብሮችን መፍጠር እንደምትፈልግም አብራርተዋል።

በአዋዛ የድርጊት መርሃ ግብር አማካኝነት በማደግ ላይ የሚገኙ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር በር የማግኘት መብታቸውን እውን ማድረግ በሚቻልበባቸው አማራጮች ላይ ሙያዊ ምክረ ሀሳቦችን የሚያቀርብ ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን መቋቋሙን እንደምታደንቅ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ያሉበት መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ መሰናክል ሳይሆንባቸው እኩል የማሪታይም መብታቸው መረጋገጥ አለበት የሚለው ጉዳይ ላይ መሰረታዊ የእሳቤ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ታምናለች ብለዋል።

ቀጣናዊ ትስስር ከማጠናከር እና ንግድን ከማሳለጥ አኳያም ድንበር ተሻጋሪ ትስስሮችን የሚያጎለብቱ መሰረተ ልማቶች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይገባል ነው ያሉት።

በዚህ ረገድም የልማት አጋሮች በተለይም በአፍሪካ የንግድ መሰናክሎችን የሚያቃልሉና የገበያ ተደራሽነትን የሚያሰፉ ፕሮጀክቶች ላይ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በመሰረት ልማት ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በዲጂታል ትስስር ላይ ያለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አቅርቦት ማደግ እንዳለበት መናገራቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡

በማደግ ላይ የሚገኙ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ልዩ የሆነ ችግራቸው እንዲፈታ እና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ትብብር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በአዋዛ የድርጊት መርሃ ግብር የማሪታይም አስተዳደር አስመልክቶ የተቀመጡ ሀሳቦች ሁሉም ሀገራት እኩል የማሪታይም መብቶች ተጠቃሚ የመሆን፣ የአካባቢ ጥበቃ መብቶች እና የውሃ ሀብቶችን በጋራ የመጠቀም መብታቸው መጠበቅ ጋር መጣጣም አለበት ብለዋል።
የባህር በር የማግኘት መብት ላይ የሚሰሩ ተቋማት ሀገራትን በእኩልነት እንዲያስተናግዱም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የአዋዛ የድርጊት መርሃ ግብርን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ማዕቀፎች እንዲተገበሩ በቁርጠኝነት ትሰራለች ያሉት ሚኒስትሩ ÷ ሌሎች ሀገሮችም ለማዕቀፎቹ ተፈጻሚነት አብክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.