ብሄራዊ ባንክ የንግዱ ማህበረሰብ ኢመደበኛ የውጭ ምንዛሪ ገበያን ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የንግዱ ማህበረሰብ ኢመደበኛ የውጭ ምንዛሪ ገበያን ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳሰቡ፡፡
አቶ ማሞ የውጭ ምንዛሪ ገበያ እንቅስቃሴን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደ አስፈላጊነቱ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ማካሄዱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ይህ የሚሆነውም ባለፈው ዓመት የባንኩ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት መጠን በሶስት እጥፍ በጨመሩ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ይህ አበረታች ሁኔታ በአዲሱ በጀት ዓመት በመቀጠሉና የማዕከላዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ፍሰትና ግኝት ከተጠበቀው በላይ በማደጉ ነው ብለዋል፡፡
ከውጭ ምንዛሪ ገቢ ከፊሉን ለባንኮች በጨረታ ማቅረቡ በባንኮች ዘንድ የሚኖረውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከማሳደግ ባለፈ የዋጋንና የውጭ ምንዛሪ ለማረጋጋት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በትናንትናው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ 28 ባንኮች ተሳትፈው 150 ሚሊየን ዶላር የተሸጠ ሲሆን÷ ሁሉም የተሳተፉ ባንኮች የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ በአማካይ አንድን ዶላር በ138 ብር ዋጋ እንዳገኙ አመልክተዋል፡፡
ባንኮቹ በሚቀጥለው ሳምንት የውጭ ምንዛሪን በበቂ ሁኔታ ለደንበኞቻቸው እንደሚያቀርቡም ነው ያስገነዘቡት፡፡
አሁን ላይ ሁሉም ባንኮች በየወሩ 500 ሚሊየን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ለንግዱ ማህበረሰብ እንደሚሰጡ ጠቁመው÷ለግል ዘርፍ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሪ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንደሚገኝ ጠቀሰዋል፡፡
ሁሉም ባንኮች ከዛሬ ጀምሮ በቀጣይ ቀናት በቂ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያቀርቡ እያሳወቁ ነው ያሉት አቶ ማሞ÷ የንግዱ ማህበረሰብ እድሉን እንዲጠቀም ጠይቀዋል፡፡
አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ለሚፈልጉ የውጭ መንገደኞች ደግሞ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እና ንግድ ባንክ ጋር በመሄድ ያለ ምንም ችግር እንደሚያገኙ አስገንዝበዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ ለውጭ ምንዛሪ ፋላጎት መደበኛውን የባንክ ሥርዓት መጠቀም እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ ማሞ÷ በህገ ወጥ ምንዛሪ ላይ የሚሳተፉ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡
ነጋዴዎች ወደ ትይዩ የውጭ ምንዛሪ ገበያ የሚሄዱት ከባንኮች በቂ ምንዛሪ ስለማያገኙ እንደሆነ እንደሚያነሱ ጠቁመው÷ አሁን ላይ መሰል ቅሬታዎች በአብዛኛው መፍትሄ አንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
ከአስመጪዎች በኩል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሲፈቅዱ ከኤል ሲ ዋጋ በላይ በብር ተቀማጭ ይጠይቃሉ ለሚለው ቅሬታም አሁን ላይ ባንኮች እንደዚህ አይነት አስገዳጅ ጥያቄ እንደማያቀርቡ አረጋግጠዋል ብለዋል፡፡
መሰል ጥያቄ የሚያቀርቡ ሕገ ወጥ ባንኮች ካሉ ለብሄራዊ ባንክ ጥቆማ ማቅረብ እንደሚቻል ጠቅሰው÷ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን በጥቂት ቀናት ለመስጠት እንደሚሰሩም አመልክተዋል፡፡
ስለሆነም ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ የመደበኛ ባንክ ሥርዓት በማይጠቀሙ አካላት ላይ እስከ መውረስ የሚደርስ ርምጃ እንደሚወስድ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተጀረው የውጭ ምንዛሪ ሪፎርም በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ታማኝነት ለመሸርሸርና የገበያ ዋጋን ለማዛበት በሚሰሩ መቀመጫቸውን ውጭ ሀገራት ያደረጉ ህገ ወጥ ገንዘብ አስተላላፊዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ