የትራንስፖርት ዘርፉ የበሽታ ምንጭ መሆን የለበትም – አቶ በረኦ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዜጎቻችን በሽታ የሚያመርት የትራንስፖርት ዘርፍ ይዘን መቀጠል አንችልም አሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በረኦ ሀሰን።
ሚኒስትር ዴዔታው ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያ ለዜጎች ምቹ የሆኑ ዘመናዊ ከተሞችን እየገነባች በመሆኗ የትራንስፖርቱን ዘርፍም አካባቢን የማይበክል ማድረግ ያስፈልጋል።
የከተሞች ትራንስፖርትን ከብክለት የፀዳ ለማድረግ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ አቅጣጫ ቀይሳ እየተገበረች መሆኗን ጠቅሰው÷ ይህንን ሙሉ ለማድረግ ከካርበን ልቀት ነጻ የሆነ የትራንስፖርት ዘርፍ መፍጠር እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
የትራንስፖርት ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ14 በመቶ እስከ 47 በመቶ የካርበን ልቀት አበርክቶ ያለው ዘርፍ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
ዘርፉ እያንዳንዱ የሕይወት ኩነት የሚከናወንበት እና ኢኮኖሚው የሚሳለጥበት እንደመሆኑ መጠን እንቅስቃሴ ሲበዛ የካርበን ልቀት መጠኑ ለአካባቢ ብክለት መንስኤ እንደሚሆን አንስተዋል።
ይህንን መቀነስ የሚቻለው በታዳሽ ሃይል ላይ በትኩረት በመስራት እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እያበረታታች ነው ብለዋል።
መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከቀረጽ ነጻ እንዲገቡ ከማድረግ ጀምሮ በሀገር ውስጥ የሚገጣጥሙ አካላትን እያበረታታ ይገኛል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፡፡
ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል እምቅ አቅም ያላት በመሆኗ ከምትፈተንበት የነዳጅ ጥገኝነት መላቀቅ ይኖርባታል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን የሚጨምሩ መንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ መኪኖችን ከእንቅስቃሴ ማስወጣት እና አሮጌ መኪኖችን በአዲስ መተካት በሚያስችሉ መፍትሄዎች ላይ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የኤሌክትሪክ መኪኖች መንቀሳቀስ እንዲችሉ በ50 ኪሎ ሜትር ልዩነት ብዙ መኪኖችን በአንድ ጊዜ ቻርጅ ማድረግ የሚያስችሉ ጣቢያዎችን ለማቋቋም እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታው ከፋና ፖድካስት ጋር የነበራቸውን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ – https://www.youtube.com/watch?v=UPSUvdaJU84
በብርሃኑ አበራ