የኢትዮጵያን የዲጂታል ዘርፍ ኢንቨስትመንት የሚያስተዋውቅ ኤክስፖ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሚስተዋውቅና ባለሃብቶችን ለመሳብ የሚያግዝ ኤክስፖ ሊካሄድ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ አቢዮት ባዩ (ዶ/ር) እንዳሉት ፥ “ፊውቸር ቴክ አዲስ 2025” የተሰኘው ኤክስፖ ከሕዳር 19 እስከ 21 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል፡፡
ኤክስፖው በዘርፉ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ ባለሃብቶችን ለመሳብ እንደሚያግዝ አመልክተዋል፡፡
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተገኙ ውጤቶችን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል ግብዓት ለመሰብሰብና ቀጣዩን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሄኖክ አሕመድ በበኩላቸው ፥ ኤክስፖው በስታርት አፕ አዋጅ መሰረት ሀሳብና ትጋት ያላቸው ወጣቶች ወደ ምርትና ተግባር እንዲቀይሩ የሚያስችሉ ዕድሎችን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በኤክስፖው ላይ ኩባንያዎች፣ ኤምባሲዎች፣ ባለሃብቶችና የሀገር ውስጥ ስታርት አፖች የሚሳተፉ ሲሆን፥ በቀጣይነት በየሁለት ዓመቱ እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል።
ኤክስፖውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክና አር ሲ ኤን ዲሲ ኮንሰልት ጋር በመተባበር ያዘጋጁታል፡፡
በመራኦል ከድር