የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት መግለጫ
እኛ የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 02 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረግነው መደበኛ ስብሰባ በዓለማዊ፣ አህጉራዊ፣ ቀጣናዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር ተወያይተናል።
ምክር ቤታችን አሁን ባለው የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ስለሚከበርበት መንገድ ተመልክቷል፡፡ በመደመር መንገድ ወደ ብልጽግና ለመድረስ እየተደረገ ስላለው ጥረትም ገምግሟል።
በዓለማችን ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ለሀገራችን ዕድልና ፈተና ይዘው መምጣታቸውን የተመለከተው ምክር ቤቱ፣ ፈተናዎችን በመሻገርና ዕድሎችን በመጠቀም ይበልጥ የሀገራችንን ጥቅም ስለምናስጠብቅባቸው ስልቶች በስፋት ተነጋግሮ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
እንደሚታወቀው፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የገጠመንን ጦርነት በአሸናፊነት ተወጥተናል። በአሸናፊነት መወጣት ብቻ ሳይሆን፣ ወታደራዊ ድላችንን በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ቋጭተናል። ዳሩ ግን ይፈልጉት የነበረው የተራዘመ ጦርነት በስምምነቱ የተጨናገፈባቸው ጠላቶቻችን ሌሎች ስልቶችን ወደ መሞከር ገብተዋል።
ምንም እንኳን እንዳሰቡት እየሆነላቸው ባይሆንም፣ እነዚህ አካላት በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን በመጠቀም የመንግሥትን ኃይልና የሕዝብን አንድነት ለመከፋፈል ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በታሪካዊ ጠላቶቻችን መሪነት እና አስተባባሪነት፣ በአንዳንድ ባንዳ ጽንፈኞች መሣሪያነት ዛሬም ጠላቶቻችን የጦርነት አምሮታቸው አልቆመም።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ጠላቶቻችን የሕዝብንና የመንግሥትን አንድነት ለመፈታተን ሁለት መንገዶችን ተጠቅመው ነበር። አንደኛው በየአካባቢው ግጭትን ማበራከት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በዲጂታል ሚዲያ መንግሥትን ማሳጣት ነው። ነገር ግን በሁለቱም ዘመቻዎች እንዳሰቡት አትራፊ መሆን አልቻሉም። ኢትዮጵያን የማዳከም ዕድላቸው እየጠበበ ነው። ባለንበት ልንከስም እንችላለን የሚለው ሥጋታቸውም ጨምሯል።
ዛሬ ያለነው ትውልድ፣ ከታሪካዊ ስብራቶቻችን እና ከዓለም ነባራዊ እውነታ ተምረናል። እንደ ድሮው በተቀደደልን ከመፍስስ ይልቅ፣ ብሔራዊ አንድነታችንንና ተቋማዊ ዐቅማችንን ለማጠናከር እየሠራን ሲሆን ይሄም ተጋላጭነታችንን በእጅጉ ቀንሶታል። ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ብሔራዊ ራዕያችንን ማሳካት የሚችል ብሔራዊ ዐቅም መገንባታችን ይቀጥላል።
ከሁሉ በላይ አዲሱ ስልታችን ሰላማዊ የፖለቲካ ዕድሎችን አሟጥጦ ይጠቀማል። ተግዳሮቶች በበረቱባቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት፣ በሁሉም መስክ ድል አስመዝግበናል። በተለይም በሦስት ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥተናል፡-
• ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በተግዳሮቶች ሳይበገሩ አንሠራርተዋል። ይሄም ውስጣዊ ተጋላጭነታችንን አጥብቦ፣ ባንዶችን ቦታ አሳጥቷል።
• በዓባይ ላይ ተገቢውንና ሕጋዊውን ተግባር በማከናወን በቀጣናው ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመናችንን ለውጠናል።
• የባሕር በር የማግኘት ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችንን ዓለም አቀፍ አጀንዳ አድርገነዋል። በዚህም በቀይ ባሕር የነበረንን ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና ለመመለስ ከአንድ ምዕራፍ በላይ ተራምደናል።
ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦቻችን በተግዳሮቶች ሳይረቱና ሳይዋጡ በስኬት እየተራመዱ ናቸው፡፡ ለውስጣዊ ተጋላጭነታችን መነሻ መሆናቸው ቀርቶ፣ ወደ ብሔራዊ ዐቅምነት ተቀይረዋል። ውስጣዊ ስንጥቃቶችን በሽብልቅ እያሰፉ፣ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብረው ኢትዮጵያን ለመውጋት ለሚተባበሩ ባንዳዎች፣ ብሔራዊና ብሔረሰባዊ አጀንዳ አሳጥተናቸዋል። ፖለቲካችን ማንነትን ከሚያጫርተው የፖለቲካ ገበያ እንዲወጣ አድርገነዋል። በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ ተመሥርቶ ብልጽግናን በሚያረጋገጥ መንገድ ቀይሰነዋል።
በአንድ በኩል በጀመርናቸው ተቋማዊ ሪፎርሞች እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሀገራችንን ውስጣዊ ዐቅም አጠናክረናል። በሌላ በኩል ደግሞ የጂኦፖለቲካውን ቅኝት በሚገባ በመገንዘብ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች አስከብረናል።
ኢትዮጵያ ያለ ጥርጥር እያንሠራራች ነው። በዓይን አይቶ፣ በእጅ ነክቶ፣ በመረጃ አጣርቶ፣ በመስክ ተሠማርቶ፣ ይሄንን እውነት ማረጋገጥ ይቻላል። ከሀገራዊ እስከ ዓለማዊ መድረኮች ለዚህ ስኬት ሚልዮን ምስክሮች አሉ። ይህ ግን ለታሪካዊ ጠላቶቻችንና ለእነርሱ ተላላኪዎች የሚዋጥላቸው አይደለም። ስለዚህም ኢትዮጵያን ከመንገዷ ለማስቀረት የመጨረሻውን ሙከራ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በዚህ የመጨረሻ ሙከራቸው ስድስት ስልቶችን ለመጠቀም እንደተነሡ ምክር ቤታችን ገምግሟል። እነዚህም ለግድያ የሚፈላለጉ ኃይሎችን በጥቅም ማስተሣሠር፤ ኢትዮጵያን በሑከት ውስጥ ማቆየት፤ በመልካም አስተዳደር ችግር የተነሣ የሚፈጠሩ የሕዝብ ቅሬታዎችን ለዐመጽ መጠቀም፤ ብሶት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን ማራገብ፤ ሚዲያዎችን የሑከት መቀስቀሻ መሣሪያ ማድረግ፤ እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ እና በሸቀጦች በኩል የኢኮኖሚ አሻጥርን መሥራት ናቸው።
ይሄንን የታሪካዊ ጠላቶቻችን የመጨረሻ ሙከራ ለመጨረሻ ጊዜ ለማምከን እኛ የብልፅግና ምክር ቤት አባላት በቃልም በተግባርም ዝግጁ፣ ቆራጥና ውጤታማ መሆን እንዳለብን ተገንዝበናል። በዋናነትም በሚከተሉት ሰባት ጉዳዮች ላይ ከሚጠበቅብን በላይ ለማከናወን ቆርጠን ተነሥተናል።
• ግጭትን ሊያስቀሩ የሚችሉ ሰላማዊ አማራጮችን በሁሉም አቅጣጫ ለመሞከርና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ለሚወስኑ ታጣቂዎች አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ፤
• የሰላምን አማራጭ ባለመቀበል በሕዝብና በሀገር ንብረት ላይ ችግር ለመፍጠር በሚነሡ ኃይሎች ላይ በተጠናከረ መንገድ ሕግ ለማስከበር፤
• በየደረጃው የሚነሡ የሕዝብ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን በኢትዮጵያ ዐቅም ልክ በየደረጃው ለመመለስ፤
• ተገቢውንና እውነተኛውን መረጃ ለሕዝብ በየጊዜው ለመስጠትና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማጋለጥ፤
• በየተቋማቱ ተመድበው የዲሲፕሊን ጉድለት፣ሙስናና የአስተዳደር በደል የሚያደርሱ የሥራ መሪዎችንና አገልጋዮችን ለመታገል፤
• በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ እንደዚሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመርናቸውን የልማት ሥራዎች የበለጠ ስኬታማ በማድረግ፤ የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን ለውጤት በማብቃት፤ የሕዝብን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ የከተማና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ፤
• በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች በሁሉም መንገድ ለማስከበር፤ ከመግባባት ላይ ደርሰናል።
በአጠቃላይ እኛ የብልፅግና ምክር ቤት አባላት፣ የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ከታቀደለት ጊዜ ፈጥኖ እንዲሳካ ለማድረግ “መመከት፣ መትጋትና ማጥራት” በሚል መርሕ ቀጣዩን ተግባራችንን ለማከናወን ወስነናል። የጠላቶቻችንን ፈተና እና ሤራ እንመክታለን። የኢትዮጵያ ብልጽግና በሁሉም መስክ እንዲሳካ ከወትሮው በበለጠ እንተጋለን። ለብልጽግና ጉዟችን ዕንቅፋት የሚሆኑትን አስተሳሰቦች፣ ባህሎች፣ ልማዶች፣ ሠርጎ ገቦች እና ባንዳዎች ደግሞ ተግተን እናጠራለን።
እኛ የምንወደው ሀገር፣ የምንቆምለት ሀገራዊ ዓላማ እና ሕልም አለን። የምናገለግለው ሕዝብ አለን። የምንገነባው ሀገር አለን። የሚናስከብረው ብሔራዊ ጥቅም አለን። ጠላት ደግሞ እነዚህን ሁሉ ማጥፋት፣ ለማፍረስና ለማሰናከል ይፈልጋል። ማልማት፣ መገንባት እና ማጽናት፤ ከማጥፋት፣ ከማደናቀፍ፤ ከማሰናከል እና ከማፍረስ በላይ ዐቅምና ትጋት ይጠይቃል።
ድል እና ኢትዮጵያ የተሣሠሩ ናቸው። ነገር ግን ከድሎች ሁሉ የሚበልጥ ድል አለ፡፡ እሱም ድልን በአነሰ ኪሣራ ማረጋገጥ እና ከዘላቂ ውጤት ጋር ማስተሣሠር ነው። ከድል ሁሉ የሚበልጠው ድል፣ ድልን ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂያዊ ግብን ጭምር ማረጋገጥ ነው። ዘላቂ ድል ማለት ውስጣዊ ባንዳዎችን ብቻ ሳይሆን ውጫዊ ጠላቶችን ጭምር ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ መርታት ነው።
ብልጽግና ብዝኃ ዐርበኝነትን ይጠይቃል። የደም ብቻ ሳይሆን የላብ መሥዋዕትነትን ይጠይቃል። ዐርበኝነት እና ዝግጁነት የሀገርን ታሪክ ይቀይራሉ። እኛ የብልፅግና ምክር ቤት አባላት ራሳችን ተግተን ሕዝብንም ለማትጋት ተነሥተናል። ራሳችን ጠርትን ሕዝቡንም ለማጥራት ወስነናል። እንደ ዐርበኛ አመራር በልካችን ለመታገል ቆርጠናል። የብልፅግና አመራር የኢኮኖሚም የግንባርም ዐርበኛ ነው። ሕዝብን ያስተባብራል። በግንባር ይፋለማል። ደጀኑንም ያጠናክራል። እኛም ይሄንን ከወትሮው በበለጠ ለመፈጸም ቃላችንን በድጋሚ እናድሳለን።
ዘመናችን ብዝኃ ታታሪነትን ይጠይቃል። ዓለም ተለዋዋጭ እና ብዙ ቀውስ አለበት። ሀገራችን ዘርፈ ብዙ የሕዝብ ፍላጎቶችና ችግሮች አሉባት። እንዲሁም የተለያዩ አደናቃፊ ኃይሎች ይፈትኗታል። እንዲህ ባለ ጊዜና ሁኔታ አመራርነት ዘርፈ ብዙ ብቃቶችን እና ታታሪነቶችን እንደሚጠይቅ ተረድተናል። ታሪካዊ ጠላቶቻችን እና ውስጣዊ ባንዳዎች ኢትዮጵያን ለማዳከም ቆርጠው ተነሥተዋል። በዚህ ወቅት በአንድ በኩል የጠላትን ጥቃት መከላከል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዘላቂ ግቦቻችንን እና ዓላማዎቻችንን መተግበር እንደሚያስፈልገን በዝርዝር ተነጋግረን ወስነናል። በየደረጃው ያለን አመራሮች በአንድ ጊዜ ብዙ ተግባራትን የምንፈጽም መሆን እንዳለብን የተግባባን ሲሆን፤ ጠላትን ስንከላከል እና ጸጥታን ስናስከብር ከልማት የምንደናቀፍ መሆን የለብንም።
ብልፅግና ብዝኃነታችንን ያከበረ፤ አንድነታችንን ያስተሣሠረ ፓርቲ ነው። ከትናንት የተማረ ነገን ያሣመረ ትርክት ያነገበ ፓርቲ ነው። የጠላትን አፍራሽ ትርክት ለመመከትና የእኛን ትርክት ለማጋባት ዲጂታል ዐርበኝነትን በሚገባን ልክ እንጠቀማለን። ጠላት የሀገርን አንድነት ለማፍረስ እና ብልጽግናዋን ለማደናቀፍ በበቀል ስሜት አፍራሽ ትርክት ሰንቆ ተነሥቷል። እኛ ማንነታችን የተሣሠረበትን እና ርዕያችን የተሰነቀበት ትርክታችንን ለሕዝብ ለማጋባት ዐርበኛ ልንሆን ወስነናል።
ሕዝብን እያማረሩ ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ እና የሕዝብን ርካታ ለመጨመር በትኩረት እንሠራለን። የሕዝብን የቅሬታ ምንጮች በመለየት እንፈታለን። የሕዝብን ቅሬታ በመስማት፣ በዕቅድና በክትትል ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንተጋለን። ሕዝባዊና ብሔራዊ ለሆነው ዓላማችን ውስጣዊ ዕንቅፋት የሆነው ሠርጎ ገብነትን እናጠራለን፤ ብሔርተኝነትን እንገራለን፤ ሌብነትንና ሕዝበኝነትን ለማጥፋት እንታገላለን። በውጭና በሀገር ውስጥ የሚኖረው የውጭ ምንዛሬ እንቅስቃሴ በሀገር ፍቅር ስሜት እንዲንቀሳቀስ በማድረግ፣ እንዲሁም የሸቀጦችን ዝውውር ጤናማነት በማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚሠሩ የውጭና የውስጥ ጠላቶችን እንታገላለን፡፡
ከዚህም በተጨማሪ መጪው ሰባተኛ ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ሕጋዊ፣ እና የሕዝቡ ምልዐተ ተሳትፎ የሚንጸባረቅበት እንዲሆን እንደ ብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባል ብሎም እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በንቃት እንሳተፋለን።
ከላይ የገለጽናቸው ውሳኔዎቻችንና ቃል የገባናቸው ግቦች ተሳክተው የኢትዮጵያን ብልጽግና በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለመመሥረት እንድንችል፣ መላው የብልፅግና አባላትና ኢትዮጵያውያን በኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ እናደርጋለን።
የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት
ነሐሴ 02 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ