Fana: At a Speed of Life!

የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላትን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የሻደይ፣ አሸንድዬ ፣ ሶለል፣ ቡሄና እንግጫ ነቀላ በዓላትን ባሕላዊ እሴቶቻቸውን በጠበቀ መልኩ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል አለ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፡፡

ከመጪው ነሐሴ 13 ቀን እስከ መስከረም 1 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚከበሩት በዓላቱ እሴታቸው ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡

በዓላቱ በታሪክ ሒደት የተቀረጹ ሚሊየኖች በገጉት የሚጠብቋቸውና የሚታደሙባቸው ሃብቶች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

በዓላቱ በሚከበሩበት አካባቢ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት በመፍጠር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከአሁን ቀደም የቡሄ፣ የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና የእንግጫ ነቀላ በዓላት በክልል ደረጃ በማክበርና በማስተዋወቅ ከፍተኛ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል።

በዚህ ዓመትም ቡሄን በደብረ ታቦር ከተማ፣ ሻደይን በዋግኽምራ፣ አሸንድዬን በሰሜን ወሎ ላሊበላ አካባቢ፣ ሶለልን በሰሜን ወሎ ራያና ቆቦ አካባቢ፣ የከሴ አጨዳና እንግጫ ነቀላ በዓላትን በምስራቅ ጎጃም በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በዓላቱ በአግባቡ ለምተው ወደ ቱሪዝም ገበያው እንዲገቡ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ነው ኃላፊው የገለጹት።

የበዓላቱ አከባበር ሥነ ሥርዓት ማጠቃለያ መርሐ ግብርም በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.