በኬንያ በትራፊክ አደጋ የ21 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኬንያ ኪሱሙ በዛሬው ዕለት በተከሰተ የትራፊክ አደጋ የ21 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
አደጋው ከቀብር ሥነ ሥርዓት ሲመለሱ የነበሩ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ ኮፕቲክ ከተሰኘ አደባባይ ላይ በመገልበጡ ነው የተከሰተው፡፡
በዚህም ከቀብር ሥነ ሥርዓት ሲመለሱ የነበሩ የ21 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አካባቢውን ፖሊስ ጠቅሶ ኬንያ ታይምስ ዘግቧል፡፡
በተጨማሪም የስምንት ወር ሕጻንን ጨምሮ በ20 ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ ነው የተገለጸው፡፡
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሚገኝና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተጠቁሟል፡፡
በሶስና አለማየሁ