Fana: At a Speed of Life!

ከ65 ሺህ 500 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሰዋል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከ65 ሺህ 500 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች በተሃድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል አለ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ ግጭትን ሊያስቀሩ የሚችሉ ሰላማዊ አማራጮችን በሁሉም አቅጣጫ ለመሞከርና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ለሚወስኑ ታጣቂዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወሳል፡፡

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ የፓርቲው ውሳኔ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊና ምርታማ ህይወት ለማሸጋገር ለሚደረገው ጥረት መሳካት ምቹ መደላደል ይፈጥራል፡፡

ኮሚሽኑ በሰላም ስምምነት እንዲሁም በመንግስት፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በሀይማኖት አባቶች የቀረቡ ጥሪዎችን ተቀብለው ወደ ሰላም የሚመጡ የቀድሞ ተዋጊዎች የሀገሪቱ የሰላምና የልማት ኃይል እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

ከህዳር 2017 ዓ.ም ወዲህ ከ65 ሺህ 500 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን የተሃድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡

ከእነዚህም ውስጥ 53 ሺህ 319 ያህሉ በትግራይ ክልል ሲሆኑ፥ በኦሮሚያ ክልል 5 ሺህ 365፣ በአማራ ክልል 5 ሺህ 168 እንዲሁም በአፋር ክልል 1ሺህ 712 መሆናቸው መግለጫው አመልክቷል፡፡

በተሃድሶ ማዕከላት ከፌደራል መንግስትና ከክልሎች ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ እንደተደረገ ጠቅሶ፥ የቀድሞ ተዋጊዎች በተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ እየተደረገ መሆኑንም አንስቷል፡፡

በትግራይ ክልል በሶስት ማዕከላት የቀድሞ ተዋጊዎችን ተቀብሎ በተሃድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በየትኛውም አካባቢ ያሉ ታጣቂዎች የህዝብንና የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው የተሃድሶ መርሐ ግብሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.