ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለግል ኢንቨስትመንት ያለው ሚና…
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም ወር የምታስመርቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት የጀርባ አጥንት ነው አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የውሃ ኢንቨስትመንት ጉባኤ በሚኒስትሮች ከፍተኛ የፓናል ውይይት ላይ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ በማጠናቀቅ ላይ ያለችውን ታላቁ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቱ ፋይናንስ ስለተደረገበት ሁኔታ ተሞክሮዋን እንድታካፍል ተጠይቀዋል፡፡
በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ቀደም ባሉት መንግስታት ዘመን እንዲጀመር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን የበጀት ድጋፍና ብድር ጠይቃ ማግኘት ባለመቻሏ ቀጣዩ ትውልድ እንደሚሰራው በማመን የዛሬውን ትውልድ እንዲጠብቅ ተገድዷል ነው ያሉት፡፡
ግድቡ በዋናነት በመንግስት አቅም እንዲሁም በሀገር ውስጥ እና ባህር ማዶ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ አባላት ቀጥታ ተሳትፎ የተገነባ የአፍሪካ ኩራትና የኃይል ምንጭ ፕሮጀክት መሆኑን ሀብታሙ (ዶ/ር) አስተድተዋል።
ግድቡ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ከ5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው አንስተው÷ በግድብ ግንባታ ሥራ የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች በቀጥታ በመሳተፍ አሻራቸውን ያስቀመጡበት ከኃይል ምንጭነት በዘለለ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ዋና ምሰሶ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በዋናነት በግሉ ዘርፍ ላለው ክፍለ ኢኮኖሚ ትልቅ የኢንቨስትመንት ዕድል ይዞ ይመጣል ያሉት ሀብታሙ (ዶ/ር)÷ ለዚህ ማሳያው በዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ የውሃና ኃይል አቅርቦት የጀርባ አጥንት ሆነው ለሌሎች ግቦች በአማካኝነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን በአጽንዖት አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትሥሥርን በመፍጠር ረገድ በቀዳሚነት ሚናዋን እየተጫወተች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ማብራራያውን ተከትሎ በጉባኤው ላይ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ከሚኒስትሩ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡