የውጭ ምንዛሪ ወጪ የሚያስቀሩ 96 ዓይነት ምርቶች …
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውጭ ምንዛሪ ወጪን የሚያስቀሩ 96 ዓይነት ምርቶች በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ነው አለ፡፡
በሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጽ/ቤት ሃላፊ አያና ገብሬ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ መንግስት ገቢ ለማሳደግና የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለመቀነስ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ሰጥቷል።
በዚህም በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ወደ ሀገር ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት መጀመሩን ገልጸው፤ በዚህም 96 ምርቶች ተለይተው በተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እየተመረቱ ነው ብለዋል።
ምርቶቹ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን እና በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቀጣይ ለተሻለ ውጤት ሚኒስቴሩ ከሚሰጠው ድጋፍ ባለፈ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል፡፡
በተካልኝ ኃይሉ