Fana: At a Speed of Life!

የመደመር መንግስት መጽሐፍ ከውጤትና ከተጨባጭ ልምድ የተቀዳ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግስት መጽሐፍን ይበልጥ አስፈላጊና ጠቃሚ የሚያደርገው ከውጤትና ከተጨበጭ ልምድና ተሞክሮ የተቀዳ መሆኑ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት በተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው ዙሪያ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ የመደመር ጽንሰ ሃሳብ በግል ሕይወታቸው ለረጅም ጊዜ የተለማመዱበትና በሰሩባቸው ተቋማት ተጠቅመውበት ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑን አስረድተዋል፡

የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ሃሳብ በተለያየ ደረጃ ማለትም በግለሰብም ሆነ በቡድን አሊያም በተቋም ደረጃ ሊተገበር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የመደመር ጽንሰ ሃሳብ ከውስን ሥፍራዎች አልፎ ወደ መንግስት ሃሳብና አቋም ያደገው በሒደት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ሃሳቡን የወል በማድረግ በብዙዎች ዘንድ ቅቡል እንዲሆን ከስልጠና ባለፈ በውይይቶች፣ በትችቶችና በመረጃዎች እንዲዳብር ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

መጽሐፉ ታሪክን የሚዳስስ፣ ወደ ፊት በመራመድ የዓለምን የነገ ሁኔታና የእኛን በነገ ውስጥ ያለን ጉዞ እንደሚተነትንም ጠቅሰዋል፡፡

መጽሐፉን ይበልጥ ጠቃሚና አስፈላጊ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ ከውጤት፣ ከተጨበጭ ልምድና ተሞክሮ የተቀዳ መሆኑ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

መጽሐፉ በሒደት ከተገኙ ልምዶች እየዳበረ፣ ሃሳብ እያጎለበተ፣ አንዳንዱም እየታረቀና እየታረመ ፍሬያማ ጽንሰ ሃሳብ እንዲሆን ዳብሮ መውጣቱን ጠቁመዋል፡፡

የመደመር መንግስት መጽሐፍ ማንኛውም ፍሬ ያለድካም እንደማይገኝ ሁሉ በብዙ ድካም መዘጋጀቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል፡፡

በኢትጵያና በአፍሪካ ታሪክ መንግስታት የሚመሩበትን ንድፍ ሃሳብ በግልጽ በዚህ መልኩ የሰነዱት ሰነድ እንዳላገኙ ጠቅሰው ÷ ስለሆነም መጽሐፉ ለብዙዎች ፈር ቀዳጅ እንደሚሆን፣ መንግስታት ምን አስበው እንዴት እንደሚሰሩ ለህዝባቸውና ለታሪክ የሚተውት ሰነድ እንደሚሆን እተማመናለሁ ብለዋል፡፡

የመደመር መጽሐፍ የመጀመሪያው ቅጽ ለአጠቃላይ እሳቤው መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመው ÷ በዚህም የመደመር ብያኔና የሰው ልጅ ፍላጎት እንዲሁም የመደመር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ሌሎች ገጾች መዳሰሳቸውን አውስተዋል፡፡

በሁለተኛው የመደመር መጽሐፍ ቅጽም ጽንሰ ሃሳቡ የወል እንዲሆን ሃሳቡን በቀላሉ በምሳሌና በነባራዊ ሁኔታዎች ለማስረዳት መሞከሩን ነው የተናገሩት፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ለመድፈቅ የተደረጉ ሙከራዎችን ለማክሸፍ እና ዋጋ የተከፈለበት ለውጥ ሀቀኛ ለውጥ ሆኖ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያመጣ አቅጣጫ የተቀመጠው በዚሁ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በለውጡ መንገድ ለውጡን ሊቀለብሱ፣ ሊጠልፉና ተሃድሷዊ በሆነ መንገድ ሊያስኬዱ የሚፈልጉ ሃይሎች እንዳሉ ተረድተን ሊደርሱብን በማይችሉት ፍጥነት ብንጓዝ አቅም እያነሳቸው እየተንጠባጠቡ ይቀራሉ በሚል በጋራ የተወሰነበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ሁለተኛው የመደመር መጽሐፍ ቅጽ ለውጡ አሸንፎ እንዲወጣ ሃሳቦች የተቀመሩበት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ሶስተኛው የመደመር መጽሐፍ ደግሞ የመደመር ጽንሰ ሃሳብ የትውልድ ሃሳብ እንዲሆንና ትውልድን በመደመር ሃሳብ እንዴት መገንባት እንደሚቻል የተመላከተበት ነው ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.