ሸማቹ ማሕበረሰብ ለሀገር ውስጥ ምርት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል – አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሸማቹ ማሕበረሰብ ለሀገር ውስጥ ምርቶች የሚሰጠውን ትኩረት ሊያጎለብት ይገባል አሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፡፡
ክልል አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ”የኢትዮጵያን ይግዙ”በሚል መሪ ሃሳብ በሀዋሳ ከተማ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡
አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የንግድ ተግባርን ማጎልበት፣ በዘርፉ ያለውን ተሳትፎ ማስፋትና ቁጠባን ባህል ማድረግ ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል፡፡
የተሻለ ሃሳብና ራዕይ በመሰነቅ ለለውጥ መትጋት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ መንግስት በዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የሀገርን እድገት ለማጎልበት አምራቾችን ማበረታታትና ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በክልሉ የሚገኙ አምራቾች ምርቶችን በተሻለ መልኩ በማምረት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ሸማቹ ለሀገሩ ምርት ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
በብርሃኑ በጋሻው