ዩክሬን በሩሲያው የኩርስክ ኒውክሌር ጣቢያ የፈፀመቸው ጥቃትና የሞስኮ ክስ…
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዩክሬን በኩርስክ ግዛት በሚገኘው የኒውክሌር ጣቢያ ላይ በሰው አልባ አውሮፕላኖች በፈፀመችው ጥቃት ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ኃይል ስምምነቶችን ጥሳለች ስትል ሩሲያ ከሰሰች።
ዩክሬን ጥቃቱን የፈፀመችው 34ኛ ዓመት የነጻነት በዓሏን እያከበረች ባለችበት ወቅት መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
በዛሬው ጥቃት የኩርስክ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው ቁጥር ሶስት ማብላያ በደረሰበት ጉዳት የአሠራር አቅሙ ወደ50 በመቶ መቀነሱን የሩሲያ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ዩክሬን ከኩርስክ በተጨማሪያ በሌሎች የሩሲያ ግዛቶች በሚገኙ በርካታ የኃይል ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ስለመፈሟም ባለስልጣናቱ አክለው ገልፀዋል፡፡
በሩሲያ ምዕራባዊ ግዛት የሚገኘው የኩርስክ ኒውክሌር ጣቢያ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የደረሰው የእሳት አደጋ ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ስለመዋሉ የኒውክሌር ጣቢያው በቴሌግራም ገፁ ባሰራጨው መልዕክት ይፋ አድርጓል፡፡
የኩርስክ ግዛት ተጠባባቂ ገዥ አሌክሳንደር ኪንሽታይን፥ ዩክሬን በጣቢያው ላይ የፈፀመችው ጥቃት ለኒውክሌር ደህንነት ስጋት እና ሁሉንም ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የጣሱ ናቸው ሲሉ ኮንነዋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት ከጥቃቱ በኋላ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባጋራው መረጃ፥ በኒውክሌር ጣቢያው ዙሪያ መደበኛ የጨረር መጠን መኖሩን አረጋግጧል፡፡
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ወደሩሲያ ግዛቶች ዩክሬን የላከቻቸውን 95 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ማክሸፉን አስታውቋል።
ሩሲያም በበኩሏ በዛሬው ዕለት 72 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና አንድ ክሩዝ ሚሳኤል ወደ ዩክሬን ማስወንጨፏን የገለፀው ደግሞ የዩክሬን አየር ሃይል ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 48 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ማክሸፉን ነው ያስታወቀው
በሌላ በኩል ሁለቱ ሀገራት በዛሬው ዕለት እያንዳንዳቸው 146 የጦር እስረኞችን መለዋወጣቸውን የዘገበው የሩሲያው የዜና ምንጭ አር ቲ ነው፡፡