የኮሎምቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሎምቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮ-ኮሎምቢያ የንግድ ትብብር ቢዝነስ ፎረም የሀገራቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተወካዮች እና የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች አባላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ፎረሙ የሀገራቱን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው ተብሏል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብረቢ በፎረሙ ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከኮሎምቢያ ጋር ያላትን የንግድ ትብብር ማጠናከር ትፈልጋለች፡፡
ኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያን ጨምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ማድረጓን ጠቅሰው፤ የኮሎምቢያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኮሎምቢያ ምክትል የንግድ ሚኒስትር ሊዊስ ፊሊፔ ኬንቴሮ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ የማጠናከር ዕቅድ እንዳላት አረጋግጠዋል።
በፈረንጆቹ 1947 የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት ኢትዮጵያና ኮሎምቢያ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም፣ አቪዬሽን እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚፈልጉ ተገልጿል።
በሰለሞን በየነ