የኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክን ትብብር አጠናክሮ ለማስቀጠል …
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ ያላቸውን የረጅም ጊዜ የትብብር ታሪክ አጠናክረው ለማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ተካሄደ፡፡
በቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የተመራ ልዑክ በቼክ ሪፐብሊክ የሚገኘውን ኦምኒፖል የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ጎብኝቷል።
በኦምኒፖል አውሮፕላን አምራች ኩባንያ በተደረገው ጉብኝት ለቱሪዝም መዳረሻዎች የሚሆኑ እና ቱሪስቶችን ማጓጓዝ የሚያስችሉ አነስተኛ አውሮፕላኖችን መመልከታቸውንም ሚኒስትሯ ገልፀዋል።
አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ እና የቱሪዝም መሰረተ ልማትን ለማሟላት ያለመ ምክክር እና ጉብኝት መካሄዱንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ ካሏቸው የትብብር መስኮች አንዱ የአቪዬሽን ዘርፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዘመናት ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚረዳ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
በአቪዬሽን ዘርፍ ከ80 ዓመት በላይ ልምድ ያለው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያው አመራሮች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።