Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ በጥራትና ፍጥነት ለመገንባት በቁርጠኝነት ይሰራል – አሊኮ ዳንጎቴ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓመት እስከ 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የሚያመርተውን ፋብሪካ በጥራትና ፍጥነት ለመገንባት በቁርጠኝነት ይሰራል አሉ የዳንጎቴ ግሩፕ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሊኮ ዳንጎቴ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት ተፈርሟል፡፡

ስምምነቱን ተከትሎ አሊኮ ዳንጎቴ እንዳሉት ÷ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ማዳበሪያ ከውጭ ታስገባ ለነበረችው ኢትዮጵያ ትልቅ ለውጥና መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ዘርፎች ጥሩ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ጠቁመው ÷ በተለይም በሀገሪቱ በቂና ዘርፈ ብዙ የግብዓት አቅርቦት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

ግዙፉ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ኢትዮጵያን ከዓለም ግንባር ቀደም አምራቾች አንዷ እንደሚያደርጋት አስረድተዋል፡፡

በዓመት እስከ 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የሚያመርተውን ፋብሪካ ÷በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በጥራት ገንብቶ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለውን ውጤት ይበልጥ እንደሚያጠናክር አስረድተዋል፡፡

ባለራዕዩ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዘርፉ እያከናወኑት የሚገኙት ዘመኑን የዋጀ ሥራ የሚደነቅ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው በ40 ወራት ውስጥ እንዲጠናቀቅ እቅድ ተይዞለታል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.