በአፍጋኒስታን የርዕደ መሬት አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ800 አለፈ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምስራቃዊ አፍጋኒስታን በተከሰተ የርዕደ መሬት አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ800 አልፏል ተባለ፡፡
በአደጋው ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ደግሞ የተጎዱ ሲሆን ሴቶች እና ህፃናት በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት አስተናግደዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ የስነ ምድር ጥናት ማዕከል እንዳስታወቀው÷ አፍጋኒስታን ከፓኪስታን ጋር በምትዋሰንበት ምስራቃዊ ክፍል በሬክተር ስኬል 6 የሚደርስ ርዕደ መሬት ተከስቷል፡፡
በአደጋው እስካሁን 812 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ የተጎጂዎች ቁጥር 3 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
የአፍጋኒስታን የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሻራፋት ዛማን÷ በአደጋው በርካታ መንደሮች ወድመዋል ብለዋል።
አደጋው ያስከተለውን ሰብዓዊ ጉዳት ለመቀነስ ፈጣን የነፍስ አድን ዘመቻ እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ለተጎጂዎች የህክምና ድጋፍ ለማድረግ የሕክምና ባለሙያዎች እና መድሃኒት አደጋው ወደተከሰተበት ኩናር ግዛት መጓጓዙንም አመልክተዋል፡፡
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር 30 ሐኪሞች እና 800 ኪሎ ግራም መድሃኒት በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ሆስፒታሎች ልኳል።
አደጋውን ተከትሎ የቻይና፣ የቱርክ፣ የአዘርባጃን፣ ህንድ እና ሌሎች ሀገራት በአደጋው የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፣ በዚህ የአደጋ ጊዜ ከአፍጋኒስታን ጎን እንደሚቆሙ ያላቸውን አጋርነት መግለፃቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ