Fana: At a Speed of Life!

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ጉብኝቴ ፕሮጀክቱ የፈራረሰ መንደር ይመስል ነበር – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲክስ ኩስመና ወደ ተሻለ ቁመና መሸጋጋሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን እንዲሆን አስችሏል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉባ ላይ ወግ በሚል ባደረጉት ቃለ ምልልስ ÷ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያና የአሁኑን ጉብኝታቸውን በቃላት አስተሳስረው በአዕምሮ ውስጥ ስዕል መቅረጽ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

ንጽጽሩ በጣም ተቃራኒ እና የሚለያይ በመሆኑም “እሳት እና ውሃ” እንደማለት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በመጀመሪያ ጉብኝታቸው የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ልክ አሁን ኮሪደር እንደሚሰራው የፈራረሰ መንደር ይመስል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ብዙው ነገር በጣም የተበላሸ ነበር፤ የተነገረንና ምድር ላይ ያለው በፍጹም አይጣጣምም፤ በዚህም በጣም አዝኜ፣ ተቆጥቼ በከፍተኛ ቁጭትና ሃዘን ስሜት ተመለስኩ ብለዋል፡፡

በአንጻሩ አሁን ላይ ግድቡ በርካታ ውስብስብ ነገሮችን አልፎ ለዚህ በመብቃቱ ከፍተኛ ደስታና ሃሴት እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጽናት እና ብቃት የሚያሳይ፣ በመሰናሰልና በመደመር ውስጥ ምን አይነት አስደናቂ ሥራ ማከናወን እንደሚችል የተማርኩበት ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ያለፉት ኢትዮጵያውያንም ሆኑ መሪዎች እንደ ሕዳሴ ግድብ ያለ ፕሮጀክት ለመገንባት ፍላጎት ነበራቸው፤ ሙከራም አድርገዋል፤ ከውጭ ሰዎች ጋር ተጻጽፈው ባለሙያ ሊያስመጡ ሞክረው እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ዓባይ ጉድ ፈላበት፣ የዓባይ መዘዝ፣ የዓባይ ጓዳ፣ የመሳሰሉ ጽሑፎች መሰነዳቸውን ጠቁመው÷ በርካታ፣ ሥነ ጽሑፎች፣ ዘፈኖች እና እንጉርጉሮዎችና ስንኞች መጻፋቸውን አንስተዋል፡፡

ለአብነትም ዓባይ በጣና ላይ ደልሎ ደልሎ ቤቱን ሰርቶ ቀረ ጊዜያዊ ነኝ ብሎ፤ ዓባይ በጣና ላይ እንዴት ቀለደበት ለአንድ ቀን ነው ብሎ ዝንታለም ሄደበት የሚሉት እና ሌሎች ሥራዎች የአሁኑ ትውልድ የደረጀ ሃሳብ እንዲይዝ አድርገዋል ብለዋል፡፡

ግድቡ ያኔ እውን ያልሆነበት የገንዘብ እጥረት፣ የቴክኒክ አቅም ውስንነት፣ የዓለም ጂኦፖለቲክስ አለመመቼት እና ሌሎች ምክንያቶች ሊነሱ እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡

አሁን ላይ እውን የሆነበት ምክንያትም የኢትዮጵያ ጂኦፖቲክስ ከኩስመና ወደ ተሻለ ቁመና እየተሸጋገረ ያለበት ጊዜ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ የነበረውን የጂኦፖቲክስ ኩስመና አንቀበልም፣ ለእኛ አይመጥንም፣ ለቁጥራችንና ለሕዝባችን ታሪክ የሚበጅ አይደለም ብለን የተሻለ ቁመና በጂኦፖለቲክስ ለመያዝ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

እነዚህ አስቻይ ጉዳዮችም የዘመናት ሕልም፣ የዘመናት ለቅሶና የዘመናት እንጉርጉሮን ወደ ፍሬ እንዲቀየር አስችለዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የሕዳሴ ግድብን ጅማሮ፣ ሒደትና አፈጻጸም ብቻ ሳይሆን ግድቡ የተገነባበት አካባቢ ፈጣሪ እጁን ታጥቦ የሰራው ነው፤ ፈጣሪ ውሃውን ብቻ ሳይሆን የት ጋር እንደምናስቀረው ሁሉ የጉባ አካባቢን አመቻችቶ የሰጠ ይመስላል ሲሉም አመስግነዋል፡፡

ፈጣሪ እንደዚህ አይነት ድንቅ ምድር ሰጥቶን ኢትዮጵያ መዝገበ ቃላት ላይ የረሃብ ምልክት እስከመባል መድረሷ ያሳዝናል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.