የቻይና አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና ጦር በዛሬው እለት ባቀረበው ወታደራዊ ትርኢት አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን ይፋ አድርጓል።
የቻይና 80ኛ ዓመት የድል በዓል በተለያዩ ወታደራዊ ትርኢቶች እየተከበረ ይገኛል።
በትርኢቱ ላይ የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ፣ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ጨምሮ የ26 ሀገራት መሪዎች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ታድመዋል።
የቻይና፣ የሩሲያ እና የሰሜን ኮሪያ መሪዎች በአንድ መድረክ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተነግሯል።
በወታደራዊ ትርኢቱ ቻይና አዳዲስ የኑክሌር ባላስቲክ ሚሳኤሎችን፣ የውሃ አካላት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ትላልቅ ድሮኖች እና ሌሎች ወታደራዊ መሳሪያዎችን ይፋ አድርጋለች፡፡
ዲኤፍ -5ሲ፣ ዲኤፍ-26ዲ፣ ዲኤፍ-61 ሚሳኤሎች እንዲሁም ጠጣር ነዳጅ ተጠቃሚ ሀገር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳኤሎች በወታደራዊ ትርኢቱ የቀረቡ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ናቸው፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ፕሬዚዳንት ሺ ሀገራቸው በጉልበተኞች ሸብረክ የማትል እና በማንኛውም ሀይል የማትበገር መሆኗን መናገራቸውን አር ቲ እና ቢቢሲ ዘግበዋል፡፡
ቻይና ከሰሞኑ የሻንጋይ ትብብር ፎረም እና የዓለም አስተዳደር ኢኒሼቲቭ መድረክን ማስተናገዷ ይታወቃል።
በሚኪያስ አየለ