የመዲናዋ ቀሪ የኮሪደር ሥራዎችን በፍጥነትና ጥራት ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመስቀል አደባባይ – መገናኛ -ሳውዝ ጌት የተከናወነውን የኮሪደር ልማት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ÷ አዲስ አበባ ወደ ቡራዩ ፣ ሰበታ ፣ ዱከም ፣ ለገጣፎ እና ሱሉልታ የሚያስወጡ አምስት ዋና ዋና በሮች እንዳሏት አንስተዋል፡፡
የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ሥራ ከመሃል መጀመሩን ጠቅሰው ÷ ወደ ዱከም የሚወስደው መውጫ እየተገባደደ ነው፤ ዛሬ የተጠናቀቀው ኮሪደርም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
ከመስቀል አደባባይ – መገናኛ – ሳውዝ ጌት የተሰራው የኮሪደር ልማት በሕንጻዎች ጥቅጥቅ ያለ በመሆኑ በጣም አስቸጋሪ ከሚባለው ውስጥ አንደኛው መሆኑን ገልጸው÷ ነገር ግን በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል ነው ያሉት፡፡
የኮሪደር ልማቱ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን÷ በሁለቱም መስመር 16 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 15 የሚጠጉ የመኪና እና የታክሲ መጫኛዎች እንዲሁም 15 ያህል መናፈሻ ቦታዎችን ያካተተ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሥራው መሳካት የከተማዋን ሕዝብ እና የከተማ አስተዳደሩ ሃላፊዎችን አመስግነው ÷ ሕዝቡ የከተማዬ ውበት እና ማማር የኔው ነው ብሎ መስራቱ የሚበረታታ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይ የአየር ብክለትን ለመቀነስ ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን እንዴት አድርገን ማሻሻል አለብን የሚለውን ማሰብ ይገባናል ነው ያሉት፡፡
የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለመለወጥ፣ ለማሻሻልና ለማዘመን እንዲሁም የተሻለ ከባቢን ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡
በቀጣይ ወደ ሰበታ እና ቡራዩ አካባቢ ያሉትን የኮሪደር ልማቶች የማስፋፋት ሥራ በጥራትና በፍጥነት ለማከናወን እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ