Fana: At a Speed of Life!

በኢጋድ አባል ሀገራት የአፈር ለምነትን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ…

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በአባል ሀገራቱ የአፈር ለምነትን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ በቁርጠኝነትና በትብብር ይሰራል አለ፡፡
የኢጋድ የአፈር ማዳበሪያና የአፈር ለምነት እንክብካቤ ማዕከል ማቋቋሚያ ሰነድ ላይ በአዲስ አበባ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
በኢጋድ የግብርናና የተፈጥሮ ሃብት ዳይሬክተር ዳሄር ኤልሚ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በአፍሪካ ያለው የአፈር ለምነት ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሰ አስጊ ሁኔታ ላይ ደርሷል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍም ኢጋድ ከዘርፉ ባለድረሻ አካላት ጋር በቁርጠኝነትና በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በተለይም የኢጋድ የአፈር ማዳበሪያና የአፈር ለምነት እንክብካቤ ማዕከል መቋቋም የአፈር ጤንነትን በማስጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አባል ሀገራቱ በዘርፉ ያላቸውን ውጤታማ የፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ እና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ተመክሮን ለማጋራት ሚናው ጉልህ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአየር ንብረት ተጽዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እና በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም አንስተዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የአፈር ሃብት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሊሬ አብዬ በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነች ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሌሎች ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች እንደምትገኝ ነው ያስረዱት፡፡
በተለያዩ ክልሎች በአሲዳማነት የተጠቃ አፈርን ለማከም ተጨማሪ የኖራ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኢጋድ በአባል ሀገራቱ የአፈር ለምነትን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ ለሚያደረገው ጥረት በንቃት እንደምትሳተፍም አረጋግጠዋል፡፡
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.