Fana: At a Speed of Life!

ለተመዘገቡት እመርታዊ ለውጦች የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አስተዋጽኦ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በለውጡ ዓመታት የተተገበሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በሁሉም መስኮች እመርታዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ አስተዋጽኦ አድርገዋል አሉ።
ጳጉሜን 3 የእመርታ ቀንን አስመልክቶ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የበላይነህ ክንዴ የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ፣ ኤ ኤም ጂ ሆልንዲንግስና ቢጃይ ኢትዮ ኢንዱስትሪያል ኤንድ ኢንጂነሪንግ ሶሉሽንስን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ በለውጡ ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች ውጤት እንዲመዘገብ መሰረት ጥሏል።
ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ በመተካትና እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ትልቅ አቅም መፍጠራቸው እየተመዘገበ ላለው እመርታ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ አምራች ዘርፉን የሚያበረታቱ አሰራሮች ተግባራዊ በመደረጋቸው ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ዋጋ የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉ እንዲነቃቃ ማድረጉን እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ እና ብድር አቅርቦትን ጨምሮ የተከናወኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለአምራች ዘርፉ መጠናከር አዎንታዊ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ያለው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ታክስ የመሰብሰብ ሀገራዊ አቅም እያደገ መጥቷል።
በ2011 በጀት ዓመት ከ200 ቢሊየን ብር በታች ገቢ መሰብሰቡን አስታውሰው፤ በ2017 በጀት ዓመት ከ900 ቢሊየን ብር በላይ የሀገር ውስጥ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፤ እመርታ ከተመዘገበባቸው የግብርና ምርቶች መካከል ቡና አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ እሴት የተጨመረበት ቡናን ወደ ውጭ የመላክ ሥራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
ለዚህም አርሶ አደሮችና በቡና ማቀነባበር ስራ ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ የማዕድን ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት የተሰጠው ትኩረት በመስኩ ውጤት ማስመዝገቡ የተመላከተ ሲሆን፤ ተቋማት ተቀናጅተው መስራታቸው በየዘርፉ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉ ተነግሯል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.