Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለ2018 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የደስታ እና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝቷል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ አዲስ ዓመት ተስፋችንን ዳግም የምናድስበትና ትስስራችንን የበለጠ የምናጠናክርበት እንደሚሆን አምናለሁ ብለዋል።

አዲሱ ዓመት ሰላም እና ብሩህ መጻኢ ጊዜን በጋራ የምንገነባበት ይሁንልን ሲሉም አምባሳደሩ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ያለው ደግሞ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ነው።

አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የእድገትና የብልጽግና እንዲሆንም ተመኝቷል።

ኤምባሲው በመልካም ምኞት መግለጫው እስራኤል በአዲሱ ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጥብቅ ግንኙነትና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለችም ነው ያለው።

በኢትዮጵያ የአርሜኒያ አምባሳደር ሳሃክ ሳርጌሲያን ለኢትዮጵያውያን እህቶችና ወንድሞቼ አዲሱ አመት የሰላምና የጤና እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ የ13 ወር ጸጋ ያላት ልዩ ሀገር ናት ያሉት አምባሳደሩ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በባህላዊ ልብሶችና ምግቦች እንዲሁም በተለያዩ የእሴት መገለጫዎችን በጋራ በመሆን የሚያከብሩበትን መንገድ አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሉክ ቡሎክ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ አዲሱ ዓመት የሰላምና የጤና እንዲሆን ተመኝተዋል።

በመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸው ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያከናወኗቸው ስራዎች ፍሬያማ እንደነበሩ አውስተዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ በንግድና ስደተኞች ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላትን ትብብር ለማጎልበት እንደምትፈልግ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ኤምባሲ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ አዲሱ ዓመት የደስታ እና የሰላም እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።

የአውሮፓ ህብረት ለ2018 የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ባስተላለፈው የመልካም ምኞት መልዕክት አዲሱ ዓመት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሰላምና የደስታ እንዲሆን ተመኝቷል።

በኢትዮጵያ የስዊድን፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊዘርላንድና ካናዳ ኤምባሲዎችም የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.