የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን ጸደቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በብራዚል በሚካሄደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) ላይ የአፍሪካውያን አጀንዳ የሚቀርብበት የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን በተሳካ ሁኔታ ጸድቋል፡፡
የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን መጠናቀቅ አስመልክቶ አፍሪካ ህብረት እና የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም በአዲስ አበባ የተካሄደው አፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አህጉሪቱ በየአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ያላትን ግልፅ አቋም በማሳየት መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡
የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎችን ማፋጠን እንዲሁም የአፍሪካን አየር ንብረት እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ በፋይናንስ መደገፍ የጉባዔው አጀንዳዎች እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡
በጉባዔው 25 ሺህ ያህል ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን÷ ከመድረኩ ጎን ለጎንም 199 በላይ ውይይቶች መካሄዳቸው ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም 43 የሚሆኑ በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አልሚዎች በጉባዔው በተካሄደ ኤግዚቢሽን ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም በብራዚል በሚካሄደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) ላይ የአፍሪካውያን አጀንዳ የሚቀርብበት የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን በተሳካ ሁኔታ ጸድቋል፡፡
የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን የተጠናከረ እና ቀጣይነት ያለው የአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ እና የአፍሪካ መር የአየር ንብረት ኢኒሼቲቮችን ማጠናከር ላይ ትኩረቱን ያደረገ የመሪዎች ስምምነት ነው፡፡
ስምምነቱ የአፍሪካ ህብረትን የአረንጓዴ ልማት እና የአፍሪካ የመሬት ገጽታን መልሶ ማቋቋም ኢኒሼቲቭ ለመደገፍ እንዲሁም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በመግለጫው ተነስቷል፡፡