Fana: At a Speed of Life!

በትጋትና በትኩረት ከተሰራ የማይቻል ነገር የለም – 589 ያመጣው ተማሪ ጎሳ ነጌሶ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የዶዶላ ኢፈ ቦሩ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ጎሳ ነጌሶ በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና 589 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡

ተማሪ ጎሳ ነጌሶ ሒሳብ 100፣ ፊዚክስ 100፣ እንግሊዘኛ 97፣ ኬሚስትሪ 98፣ ባዮሎጂ 96 እና አፕቲትዩድ 98 አምጥቷል፡፡

ተማሪ ጎሳ ነጌሶ በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 ነጥብ 11 ብቻ በመሳት 589 በማምጣቱ እጅግ መደሰቱን ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

ትምህርቴን በእቅድና በትኩረት በመከታተሌ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ችያለው የሚለው ተማሪ ጎሳ÷ አላማን ለማሳካት በትጋት ከተሰራ የማይቻል ነገር እንደሌለ ይናገራል፡፡

ለ12ኛ ክፍል ፈተና እቅድ በማውጣት በግሉም ሆነ ከጓደኞቹ ጋር በሚገባ መዘጋጀቱን ገልጾ ÷ መምህራንና ወላጆቹም ከፍተኛ እገዛ እንዳደረጉለት ጠቅሷል፡፡

በክፍል ውስጥ ትምህርቱን በትኩረት ከመከታተል ባለፈ አጋዥ መጽሐፍትን በማንበብ ያልገባውን መምህራንን ጠይቆ እንደሚረዳ ተናግሯል፡፡

ተማሪዎች ለትምህርታቸው ብቻ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ካደረጉ የፈለጉትን ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉም መክሯል፡፡

ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ልዩ ፍላጎት እንዳለው የሚናገረው ተማሪ ጎሳ ÷ በቀጣይ ኮምፒዩተር ሳይንስ በማጥናት ለሀገሩ በዘርፉ የሚጠበቅበትን ለማበርከት ማቀዱን ገልጿል፡፡

የዶዶላ ኢፈ ቦሩ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ደቱ ዲቦ በበኩላቸው ÷ ተማሪ ጎሳ ነጌሶ ትምህርቱን በሚገባ የሚከታተል፤ በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጸ በጣም ጎበዝ ተማሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተማሪ ጎሳ በትምህርት ቤቱ መምህራንም ሆነ በተማሪ ጎደኞቹ ዘንድ ተወዳጅና እና ምስጉን መሆኑንም አውስተዋል፡፡

በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና 591 በማምጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ካሊድ በሽርም የዶዶላ ኢፈ ቦሩ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.