Fana: At a Speed of Life!

የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሄ ያመላከተ ነው – አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት መጽሐፍ የኢትዮጵያን ችግሮች በጥልቅ የዳሰሰና መፍትሄ ያመላከተ ነው አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው ‘የመደመር መንግሥት’ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል።

በመጽሐፉ የምረቃ መርሐግብር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ባቀረቡት የመጽሐፍ ዳሰሳ ላይ እንዳሉት፣ መጽሐፉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሁኔታ የሚያስቃኝ ነው።

በተለይ የኢትዮጵያን ችግሮች በጥልቅ የዳሰሰና ተግባራዊ መፍትሄዎችን ያመላከተ መጽሃፍ መሆኑን ጠቅሰው፥ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

አስተሳሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ ከቁጭት የሚነሳ መጽሐፍ ነው ያሉ ሲሆን፥ ነገሮችን አፍርሶ ከመስራት ይልቅ አዎንታዊውን ማስቀጠልና አሉታዊውን ማስተካከል ላይ እንደሚያተኩር አብራርተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ለዘመናት የሄደችበትን ተቸካይ የፖለቲካ አካሄድ የቀየረ አተያይ ስለመሆኑ ገልጸው፥ ፖለቲካችንን ያሸነፈ አካል እንደፈለገ ሁሉን ይጠቅልል ከሚል አካሄድ የሚያወጣ ነው ብለዋል።

እኔ የፈለኩት ካልሆነ ከሚል የዜሮ ድምር ጨዋታ መውጣት የሚቻልበትን ዘመናዊ የፖለቲካ አካሄድ ያመላከተ መጽሐፍ መሆኑንም ነው አቶ ጌታቸው ያነሱት።

በሌላ በኩል ዜጎች ከመሰረታዊ ፍላጎት ባሻገር በክብር የመኖር ህልማቸውን ለመመለስ አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ችግሮች በነበረው አካሄድ ትርጉም ባለው መልኩ መፍታት እንደማይቻል አንስተው፣ የመደመር እሳቤ ተግባራዊ ያደረገው መፍጠርና መፍጠን በዚህ ረገድ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማን የተከማቸ ችግር ለመፍታት የተተገበረው የመፍጠርና መፍጠን መፍትሄ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆኑንም ተናግረዋል።

አዲስ አበባን ለመለወጥ የተጀመረው ስራ አዲስ የስራ ባህልን ያለማመደ መሆኑን ገልጸው፥ በቀጣይ በአዲስ አበባ የታየው አዲስ ተስፋ ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫ እንዲሰፋ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

መጽሐፉ ለማንበብ ምቹ በሆነ አቀራረብ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፥ ሁሉም እንዲያነበው ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.