የመከላከያ ሠራዊት አሁናዊ ቁመና የኢትዮጵያን ህልውና ለማይሹ አካላት መልዕክት የሚሰጥ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሠራዊት አሁናዊ ቁመና እና ዝግጁነት የኢትዮጵያን ህልውና ለማይሹ አካላት ትልቅ መልዕክት የሚሰጥ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅራቢነት ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን በሾሙበት ወቅት፤ ሹመቱ ከፍተኛ መኮንኖች ላሳዩት የስራ ጥንካሬ፣ ታማኝነትና ብርታት የተሰጠ ነው ብለዋል።
ውትድርና ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለህዝብ ክብር ህይወትን አሳልፎ ለመስጠት ቃል ኪዳን የሚገባበት ታላቅ ሙያ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጽኑ ወታደር ቋንቋው ሀገርና ህዝብን ማገልገል መሆኑን ጠቅሰው፣ የመከለከያ ሠራዊቱም በዚህ ረገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የሠራዊቱ አሁናዊ ዝግጁነት የኢትዮጵያን ህልውና ለማይሹ አካላት ትልቅ መልዕክት የሚሰጥ መሆኑንም አብራርተዋል።
መከላከያ ሠራዊት መልህቁ በሁሉም አግባብ ራስን መቻል እንዲሁም በቴክኖሎጂና ክህሎት ልቆ መገኘት መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ይህም የኢትዮጵያን ህላዊ ለማወክ በጋሻ ጃግሬነት ለመሰለፍ የሚከጅሉ ቡድኖች ባለቡት አካባቢ ትልቅ መድህን ነው ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊትን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አስማምቶ የማይደፈር እንዲሆን ቀን ከሌት ለሰሩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መንገድ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ ይህን መንገድ ለማደናቀፍ የሚሹ አካላት ደግመው ደጋግመው ሊያስቡ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።