አንድነታችንን የሚያፀኑ ዕሴቶቻችንን ተጠቅመን ብልፅግናችንን እናረጋግጣለን – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደ “ዮ ማስቃላ” ያሉ የአንድነት ግማዶቻችንን የሚያፀኑ ድንቅ ዕሴቶቻችንን ተጠቅመን ብልፅግናችንን እናረጋግጣለን አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፡፡
የጋሞ ሕዝብ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያና የዘመን መለወጫ በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ ተከብሯል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ዮ ማስቃላ የጋሞ ህዝብ የማንነቱ መገለጫ፣ የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት፣ የአብሮነትና የአንድነት ማሳያ፣ የፍትሀዊነት ሚዛን መለኪያ እንዲሁም የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የመላ ኢትዮጵያዊያን የጽናትና የአንድነት አሻራ የሆነው ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት ወቅት መከበሩ የዘንድሮውን በዓል ይበልጥ ደማቅ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ዮ ማስቃላ የጸብ እና የልዩነት ግድግዳ አፍራሽ ብቻ ሳይሆን ከጋሞ ህዝብ ጥልቅ የህይወት ፍልስፍና የሚቀዱ የሰላም፣ የደግነት፣ የመቻቻል፣ የመተባበርና የመተሳሰብ እሴቶችን ያቀፈ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ከዚህም ባለፈ ቂምና ቁርሾን የሚጸየፍ ትውልድን በማነጽ ሀገርን የማሻገር እምቅ አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፥ የበዓሉን እሴቶች ሰላምን ለማፅናትና ትብብርን ለማጠናከር መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡