ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ ኢሬቻ የምስጋና ቀን ነው፤ ይበልጡንም ምድርን በዝናብ ያጠገበው ፈጣሪ በምስጋና የሚዘከርበት በዓል ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ሕዝብ በዚህ ውብና በተስፋ በተሞላ ወቅት የክረምቱን አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፎ በሁሉም ነገር ወደተትረፈረፈ ብራ ላሻገረው ፈጣሪ ዐደባባይ ወጥቶ ምስጋና ያቀርባል ሲሉ ገልጸዋል።
ያለፈውን ዘመን ዘግቶ አዲስ ዘመን ይጀምርበታል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የምስጋና ባህል እንዲገነባ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጸና፣ ኢትዮጵያ ከሁሉም- በሁሉም- ለሁሉም እንድትሆን ኢሬቻ አንዱ ዕሴቷ ነው ብለዋል።