ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሀዲያና ስልጤ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረከቡ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን ለነዋሪዎች አስረክበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ረቡዕ በሀላባና ከምባታ ዞኖች የነበረው ሞዴል የገጠር መንደሮች ርክክብ ሥነ ሥርዓት ቀጥሎ ዛሬ በሀዲያና ስልጤ ዞኖች የተገነቡ ቤቶችን አስረክበናል ብለዋል፡፡
ባለሶስት መኝታ መኖሪያ ቤቶቹ ለማብሰል የሚያገለግል የባዮጋዝ መሣሪያ፣ የፀኃይ ኃይል ማመንጫ፣ የዶሮ ማርቢያ እና የተለየ የእንስሳት በረት የተሟላላቸው ናቸው፡፡
መርሐ ግብሩ በተመጣጣኝና አነስተኛ ወጪ ከአካባቢ በሚገኙ ግብዓቶች የተሻለ መኖሪያ ከማስገኘት አንፃር ለገጠሩ ማሕበረሰብ ብልጽግና ያለንን ሕልም የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ማኅበረሰብ አዲስ ሀሳቦች ሲፈልቁ “አይቻልም” በሚለው የቆየ አስተሳሰብ የመፈተን ተግዳሮት ይደቀንብን ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይሁንና በተጨባጭ በሚታየውና በተገኘ ውጤት ላይ ወደ አለማመንና አለመቀበል በሚመራን የሃሳብ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ የለብንም ብለዋል፡፡
ዜጎች ለውጥ እንደሚቻል ፤ ሃብቶቻችንን ወደ ትክክለኛ የቅድሚያ ትኩረቶቻችን ካዋልንም ማሕበረሰብን በርግጥም ማሻገር እንደምንችል ማመን ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በአራቱ ዞኖች የተሠራው ሥራ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች መደገም እንዳለበት አሳስበው ÷ አመራሩም ይህን ታላቅ ሥራ እንደሚፈጽም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡