በአፋር ክልል የፖሊዮ መከላከያ ክትባት መሰጠት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል 3ኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ጀምሯል።
በሎጊያ ከተማ በተካሄደው የክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ እንዳሉት÷ በዘመቻው ከ349 ሺህ 72 በላይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ለመከተብ ታቅዷል።
ዘመቻውን “አንድም ከአምስት አመት በታች የሆነ ህፃን የፖሊዮ ክትባት ሳይከተብ መቅረት የለበትም” በሚል መሪ ሀሳብ ለማካሄድ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና እና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀመዱ አህመድ በበኩላቸው÷ ዘመቻው ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3 በተመረጡ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚሰጥ አመላክተዋል፡፡
ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም ህፃናት ከዚህ በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም ክትባቱን መውሰድ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ክትባቱ ቤት ለቤት፣ በመጠለያ ጣቢያዎች፣ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እና በህፃናት መቆያዎች እንዲሁም በሌሎች ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ይሰጣል ብለዋል።
የሀይማኖት አባቶችን ጨምሮ የሚመለከታቸው ሁሉ ስለዘመቻው መልዕክት እንዲያስተላለፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በያሲን ኑሩ