ዘመን ባንክ 8 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ትርፍ አገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘመን ባንክ የባለአክሲዮኖች ማህበር 17ኛ መደበኛና 12ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዷል።
በጉባኤው ባለአክሲዮኖች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የባንኩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ጉባኤው በ2017 በጀት ዓመት በነበረው አጠቃላይ የባንኩ የስራ አፈጻጸም ላይ ተወያይቶ ቀጣይ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።
የቦርዱ ሊቀመንበር እንዬ ቢምር በጉባኤው ላይ እንደተናገሩት፤ የባንኩ አጠቃላይ ገቢ 14 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በመሆን ከፍተኛውን እድገት አስመዝግቧል።
ባንኩ በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ 5 ነጥብ 87 ቢሊየን ብር የተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡን አስረድተዋል።
ዘመን ባንክን ለዚህ ውጤት ያበቃው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጨምሮ የፋይናንስ ስርአቱ ላይ የተደረጉ ለውጦች እንደሆኑ አመልክተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት አጠቃላይ ሃብቱ 88 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መድረሱንና ተቀማጭ ገንዘቡም 64 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ሆኗል ነው ያሉት።
በሃይማኖት ወንድራድ