የጋራና የውክልና ገቢ አሰባሰብ ፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ሥርጭት እውን እንዲሆን እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራልና የክልል መንግስታት የጋራና የውክልና ገቢ አሰባሰብ ውጤታማ አፈጻጸም ፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ሥርጭት እውን እንዲሆን እያደረገ ይገኛል አሉ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ።
የገቢዎች ሚኒስቴር ከፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የገቢ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲያካሂድ የቆየውን የውይይት መድረክ አጠናቋል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ የወሰደችው የፖሊሲ ለውጥና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በገቢ አስተዳደር ስርዓቱ ላይ እመርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ እያደረገ ነው።
በዚህም ሀገራዊ ወጪን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል የታክስ አስተዳደር አቅም በመገንባት ረገድ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱ ለፌዴራል መንግስት፣ ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሰጠው ግልጽ የተግባርና ኃላፊነት እርከን መኖሩን አስረድተዋል።
ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በተፈጠረ ተግባቦት የኢትዮጵያን የታክስ አስተዳደር ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስቀጠል የሚያስችል ምኅዳር ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተወሰደው ማሻሻያ የገቢ መሰብሰብ አቅም በማጎልበት ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡