ደብረ ብርሃን ፋና ኤፍ ኤም 94.0 የሕዝብ ጥያቄዎችን በማስመለስ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ደብረ ብርሃን ፋና ኤፍ ኤም 94 ነጥብ 0 የሕዝብ ጥያቄዎችን በማስመለስ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው አለ የከተማ አስተዳድሩ።
ደብረ ብርሃን ፋና ኤፍ ኤም 94 ነጥብ 0 የተመሰረተበትን 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
መርሐ ግብሩ ከመንግስት ተቋማትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅትና በትብብር የሚሰራበትን ሁኔታ ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ ም/ከንቲባ ወርቃለማው ኮስትሬ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ጣቢያው ለአካባቢው ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ በመሆንና ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
ለከተማው ሁለንተናዊ ዕድገት ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነው÷ የሕዝቦችን አንድነትና ልማት ለማረጋገጥ በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
በጋራ በመስራታችን ተጠቃሚ ሆነናል ያሉት የንግድ ተቋማት ባለቤቶች በበኩላቸው÷ በትብብር መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ዘላለም ገበየሁ ÷ ፋና ኤፍ ኤም 94 ነጥብ 0 በአካባቢው በይዘትና በሥርጭት ጥራት ተወዳጅ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የአካባቢውን ሃብት በማስተዋወቅና የሕብረተሰብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አንስተው÷ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአላዩ ገረመው