በአፍሪካ አካታችና ጥራት ያለው የክህሎት ስልጠና ማስፋፋት ላይ በትኩረት መስራት ይገባል – ማህሙድ አሊ ዩሱፍ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ አካታችና ጥራት ያለው የክህሎት ስልጠና ማስፋፋት ላይ በትኩረት መስራት ይገባል አሉ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ።
2ኛው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት “የአፍሪካን የኢንዱስትሪ አቅም ማጎልበት፣ ለፈጠራ፣ ለእድገት እና ለዘላቂነት ክህሎት ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ነው።
ሊቀ መንበሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአፍሪካ ሀገራት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
በአኅጉሪቱ አካታችና ከፍተኛ ጥራት ያለው የክህሎት ስልጠና ማስፋፋት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የክህሎት ሳምንቱ በዘርፉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ወደ ተግባር እንዲገቡ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አህጉራዊ መዳረሻዎች ላይ በጋራ በመስራት ቀጣይነት ባላቸው የልማት ተግባራት ላይ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ህዝቦቿ ላይ ኢንቨስት የማታደርግ አፍሪካ መልማት አትችልም ያሉ ሲሆን፥ ወጣቶችን በክህሎት በማሰልጠን በመጻኢ እድሉ ላይ እንዲወስኑ ማስቻል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት