Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ነው – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ነው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ።

ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የአፍሪካ ቀንድ ኢንሼቲቭ ሚኒስትሮች ስብሰባ በዋሽንግተን ዲሲ ተካሂዷል።

በመድረኩ ኢትዮጵያ በመወከል የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ የተሳተፉ ሲሆን የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች፣ የልማት አጋር ተወካዮች እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በዚህ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ላይ የተከናወኑ ተግባራት የተገመገሙ ሲሆን፤ አሁን እያጋጠሙ ያሉ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እና ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር በሚወሰዱ የፖሊሲ ተግባራት ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ በመድረኩ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ በቅርቡም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ መቻሏን አስገንዝበዋል፡፡

ግድቡ ተፋሰሱን እና ሌሎች የጎረቤት ሀገራት በኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና ድንበር ተሻጋሪ ንግድ እንደሚያቀላጥፍ ገልጸው÷ ይህም የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ የሆነው ነፃ የንግድ ቀጠና ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል፡፡

ቀጣናዊ ውህደትን ለማፋጠን የተደረጉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው የኢኮኖሚ ትብብር አጀንዳን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ዓለም ባንክ ከኢጋድ ጋር በመተባበር ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚያደርጉትን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለአፍሪካ ቀንድ የጋራ ትብብር ቁርጠኛ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ÷ በዚህ ረገድ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.