የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባስተላለፈው የሐዘን መግለጫ ÷ ለቤተሰባቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶችና ለመላው ኢትዮጵያዊያን መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ የሕዝበ ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆኑ በምክራቸውና በተግሳፃቸው በመላው ኢትዮጵያዊያን መወደድንና ክብርን የተጎናፀፉ ታላቅ አባትና መሪ፣ የሀገር ሽማግሌና ዋርካ በመሆን ኢትዮጵያዊያንን በእምነት፣ በጎሳና በብሔር የማይነጣጥሉ አባት እንደነበሩ ጉባኤው አስታውሷል፡፡
በአንድ ወቅት ለመላው ኢትዮጵያዊያን “ሰው ሁኑ፤ ሰውነት ይቀድማል” በሚለው ምክራቸው እና ተግሳጻቸው እንደሚታወሱም ጠቅሷል፡፡
ተቀዳሚ መፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የቀድሞው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ በመሆን አገልግለዋል፡፡
የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሥርዓተ ቀብር ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው የሰጡትን አገልግሎት ታሳቢ በማድረግ ኢስላማዊ ሥርዓቱና ደንቡን በጠበቀ መልኩ በልዩ ፕሮቶኮል የሚፈፀምበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጉባኤው ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን መርሐ ግብር ለማስፈፀም ዝግጁ መሆኑን አመልክቷል፡፡