Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የግል ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግል ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር ቁርጠኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች ነው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ።
ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የገንዘብ ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) ዋና ዳይሬክተር ማክታር ዲዮፕ እና ከባለብዙ ወገን ኢንቨስትመንት ዋስትና ኤጀንሲ (ኤምአይጂኤ) ምክትል ፕሬዚዳንት ሂሮሺ ማታኖ ጋር ተወያይተዋል።
የውይይቱ ዓላማ በኢትዮጵያ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ላይ ስትራቴጂያዊ ትብብርን ማጠናከር እና የግሉ ሴክተር እድገትን ማጎልበት ነው።
አቶ አህመድ ሺዴ በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተገበረችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለባለሀብቶች ይበልጥ የተረጋጋና ሳቢ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ጠቅሰው፤ የግል ኢንቨስትመት እንዲጠናከር ቁርጠኛ አቋም እንዳላት አረጋግጠዋል።
ማክታር ዲዮፕ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ፈጣን ለውጥ በማድነቅ ተቋማቸው በኢትዮጵያ የግል ኢንቨስትመንት እንዲያድግ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
አይኤፍሲ ልማትን የሚያበረታቱ እና የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኤምአይጂኤ በመጪው ታህሳስ ወር በአዲስ አበባ የባለሀብቶች እና ፖሊሲ አውጪዎች አውደ ጥናት እንደሚያካሂድ የገለጹት ደግሞ ሂሮሺ ማታኖ ናቸው።
መድረኩ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ እና ለማሳለጥ እንድትችል አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
አይኤፍሲ እና ኤምአይጂኤ የዓለም ባንክ የግል ዘርፍ አካላት ሲሆኑ የግል ኢንቨስትመንቶችን በመደገፍ እና በዘርፉ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን የሚቀንሱ ድጋፎች የሚያደርጉ ተቋማት ናቸው።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.