Fana: At a Speed of Life!

ብርቱካን ተመስገን እና የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችን ጨምሮ 16 ተከሳሾች ላይ ምስክር መሰማት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግስት እና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ብርቱካን ተመስገን እና የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችን ጨምሮ 16 ተከሳሾች ላይ ምስክር መስማት ጀምሯል።

ዓቃቤ ሕግ ተፈጽሟል ባለው የወንጀል ድርጊት እንደየተሳትፏቸው ሦስት የተለያዩ ክሶችን መመስረቱ ይታወሳል፡፡

ተከሳሾቹ ብርቱካን ተመስገን ፣ መዓዛ መሐመድ፣ ተስፋዬ ወልደሥላሴ፣ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር እና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ አመራሮችን ጨምሮ 16 ግለሰቦች ናቸው።

በአንደኛው ክስ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተጠርጣሪዎች በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ) እና የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3/1/ለ/ ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ ሌሎች ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን የፖለቲካ ዓላማን በኃይል ለማስፈፀም በማሰብ በሕገ መንግሥት የተቋቋመውን የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥትን በኃይል በማስወገድ ስልጣን መያዝ፤ ይህ ካልሆነም መንግሥትን በኃይል በማስገደድ ለድርድር እንዲቀመጥ ማድረግ የሚል ዓላማ ይዘው መንቀሳቀሳቸው በክሱ ተመላክቷል፡፡

በዋናነትም 6ኛ ተከሳሽ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆና በዩኒቨርሲቲው ተመድባ ባለችበት ተጠልፋ እንደተደፈረች በማስመሰል፣ ሐሰተኛ መታወቂያን ጨምሮ የገንዘብ ድጋፍና ዕቅድ አውጥቶ በመስጠትና በመተግበር በመሳተፋቸው ተከሳሾቹ በፈፀሙት የሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ7ኛ እስከ 11ኛ ተራ ቁጥር ያሉ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ)፣ 34፣ 43 (3)፣ 46 እና የጥላቻ ንግግርን እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4፣ 5 እና 7/4 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ተከስሰዋል፡፡

7ኛ ተከሳሽ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር፣ 8ኛ ተከሳሽ ሲልቨር ስፕሪንግ ፕሮዳክሽን እና ፕሮሞሽን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር፣ 9ኛ ተከሳሽ ማክዳ ፍስሐጽዮን (ማክዳ አሰፋ) በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም የሕግ ክፍል አስተያየትንና የሥራ ኃላፊነቷን ወደ ጎን በመተው ትክክለኛ ያልሆነ የተቀነባበረ ታሪክ ለሕዝብ እንዲደርስ ማድረግ የሚል ተመስርቶባታል።

10ኛ ተከሳሽ የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም ዳይሬክተር ታሪኩ ኃይሌ ረታ እና 11ኛ ተከሳሽ ረዳት ዳይሬክተር ህሊና ታረቀኝ 6ኛ ተከሳሽ ብርቱካን ተመስገንን በአካል ያገኟት ሲሆን÷ የሚያጠራጥሩ እውነት የማይመስሉ ንግግሮች እያሉ በበቂ ሳያረጋግጡ ግብረአበር በመሆን የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

እንዲሁም ሦስተኛው ክስ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9 (2) በመተላለፍ በ3ኛ፣ በ6ኛ እና ከ12ኛ እስከ 16ኛ ተራ ቁጥር በሚገኙ ተከሳሾች ላይ መቅረቡ ተጠቅሷል፡፡

ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን፣ በወንጀሉ ድርጊት እና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ለ6ኛ ተከሳሽ ብርቱካን ተመስገን የማይገባትን ከ3 ሚሊየን በላይ ብር ከተለያዩ ግለሰቦች ወደ ባንክ ሒሳብ ቁጥሯ እንዲገባላት ሁኔታ በማመቻቸት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

በዚህ መልኩ ተከሳሾች በክሱ ላይ በዝርዝር የቀረበባቸውን የወንጀል ተግባር አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ 34 ምስክሮችን ማሰማት ጀምሯል።

በሲፈን መኮንን

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.