የቻይና ኢኒሼቲቮች ለአዲሱ የዓለም ሥርዓት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራት በተለዋዋጩ ዓለም ውስጥ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኢኒሼቲቮችን፣ ጉባኤዎችን እና የትብብር ፎረሞችን ያዘጋጃሉ፡፡
በምዕራቡ ዓለም ተጽዕኖ ሸብረክ ያላለችውና የአዲሱ ዓለም ሚዛን አስጠባቂዋ ቻይና የባለብዙ ዋልታ ዓለም እንዲፈጠር እንደ የተባበሩት መንግሥታት ባለ ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ለዘመናት ድምጿን አሰምታለች፡፡
የኃያልነት ፉክክሩ እየበረታ በመጣበት እና የዓለምን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ለመጠቅለል በሚደረገው ትግል ውስጥ አዳዲስ ፖለቲካዊ ርምጃዎችን እየወሰደች የምትገኘው ቻይና ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዓለም እንዲፈጠር በመሪ ተዋናይነት እየታገለች ትገኛለች፡፡
ቻይና የድንበር ደህንነት ጉዳዮችን ለመፍታት ያቋቋመችው የሻንጋይ ትብብር ፎረም በምዕራቡ ዓለም ተጽዕኖ ስር ላለመውደቅ የጀመረችው ዓለም አቀፋዊ ኢኒሼቲቭ ነው፡፡
በቻይና፣ ሩሲያ፣ ካዛኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ታጃኪስታን እና ኡዝቤክስታን የተመሠረተው ፎረሙ÷ በሂደት ህንድ፣ ፓኪስታንና ቤላሩስን አባል በማድረግ የዓለምን ሕዝብ ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ የሚወስዱ ሀገራት እና አጋሮችን መጨመር ችሏል፡፡
በአሁኑ ሰዓት 20 ሀገራት የሚሳተፉበት ትልቅ ተቋም በመሆን በመካከለኛው እስያ ላይ ያደርግ የነበረውን የትኩረት አቅጣጫ በመቀየር ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የሚነጋገርበት መድረክ ሆኗል፡፡
የቲአርቲ ወርልድ የፖለቲካ ተንታኝ ሙርሲል ዶጉሩል ዘንድሮ በተዘጋጀው የሻንጋይ ትብበር ፎረም ቻይና የእስያ እና ታዳጊ የደቡብ ሀገራት በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት ውስጥ የራሳቸውን ፖለቲካዊ አቋም እንዲይዙ ማድረጓን ይናገራሉ፡፡
ከጉባኤው ማግስት ቻይና የዓለም አቀፍ አስተዳደር ሥርዓት ይፋ ማድረጓን በማስታወስ አዲሱ ኢኒሼቲቭ ፍትሐዊ እና አካታች የዓለም ሥርዓት እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ቻይና አሁን ላይ የተሃድሶ አራማጅ እና የአዲሱ ባለብዝሃ ዓለም ሥርዓት ጠባቂ መሆኗን በመግለፅ÷ ይህንን ሚናዋን ለመወጣት ከዓለም አቀፍ ልማት ኢኒሼቲቭ እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ሰላምና ፀጥታ ኢኒሼቲቮች በተጨማሪ በሻንጋይ ትብብር ጉባኤ ማግስት የተመሰረተውን የዓለም አስተዳደር ኢኒሼቲቭ 4ኛው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ዋና ምሰሶ ማድረጓን አንስተዋል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በመጥቀስ ቲአርቲ ወርልድ እንደዘገበው÷ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ፣ ጤና፣ ቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንት እና ሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ታዳጊ ሀገራት በቂ ውክልና የላቸውም።
የቻይና አዳዲስ ኢኒሼቲቮች ዓለም አቀፋዊ ተቋማት አካታች፣ ምላሽ ሰጭ እና ፍትሐዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
ለአብነትም እንደ የአየር ንብረት፣ ዲጂታል አስተዳደር እና የኢኮኖሚ እኩልነት ያሉ ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች የጋራ ትብብር እና ማሻሻያ እንደሚፈልጉ አስነብቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!