አማዞን በኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ጉዳት የደረሰባቸውን ደንበኞች ይቅርታ ጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አማዞን ኩባንያ በትልቁ የአማዞን ዌብ ሰርቪስ መቋረጥ ምክንያት ጉዳት ያስተናገዱ ደንበኞቹን ይቅርታ ጠይቋል፡፡
አማዞን ይህ ክስተት ሰኞ ማለዳ ላይ እንደተከሰተ በመግለጽ ስርዓቶቹ በትክክል መስራት አቁመው እንደነበር ገልጿል።
በዚህም ኩባንያው ክስተቱ ደንበኞቹ ላይ ላስከተለው ተጽዕኖ ይቅርታ መጠየቁ ነው የተገለጸው፡፡
የአማዞን ዌብ ሰርቪስ አንዳንድ የዓለም ታላላቅ መድረኮችን ከመስመር ውጭ በማድረጉ ሰኞ ዕለት መጠነ ሰፊ አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ያስታወሰው ኩባንያው፤ በአገልግሎቱ መቆራረጥ የአይፒ አድራሻዎች ኮምፒውተሮችን እና ድረ ገጾችን ማገናኘት አልቻሉም ነበር ብሏል።
አገልግሎቶቻችን ለደንበኞቻችን፣ ለመተግበሪያዎቻቸው እና ለዋና ተጠቃሚዎች እንዲሁም ለንግድ ስራዎቻቸው ምን ያህል ወሳኝ እንደሆኑ እናውቃለን በማለት አስረድቷል፡፡
አንዳንድ አገልግሎቶች ከተቋረጡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ ስራ የተመለሱ ሲሆን አንዳንዶቹ አገልግሎቶች ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ተቋርጠው እንደነበር ተመላክቷል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ መቆራረጡ ቴክኖሎጂው በአማዞን ላይ ባለው የኮምፒውቲንግ ዘርፍ ምን ያህል ጥገኛ እንደሆነ ያሳያል።
ኩባንያው ከክስተቱ ለመማር እና ተደራሽነቱን ለማሻሻል የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀቱን አብራርቷል፡፡
የኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት የሶፍትዌር መሐንዲስ ጁነዴ አሊ (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የተሳሳተ አውቶሜሽን የአማዞን ችግሮች ዋና አካል ነበሩ ብለዋል።
ኩባንያዎች የበለጠ እንደዚህ ያሉ ክስተቶችን የሚቋቋሙ እንዲሆኑ ስራዎችን መስራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ