ከፈረንሳይ ሎቭር ሙዚዬም ውድ የሆኑ ጌጣጌጦችን በመስረቅ የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፈረንሳይ ሎቭር ሙዚዬም ውድ የሆኑ ጌጣጌጦችን በመስረቅ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የፓሪስ ዐቃቤ ሕግ ፅህፈት ቤት እንደገለፀው፤ ግለሰቦቹ ከሙዚዬሙ የሰረቋቸውን ውድ ጌጣጌጦች በመያዝ ከሀገር ሊወጡ ሲል በቻርልስ ደ ጎል አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በተደረገው ማጣራት አንደኛው ተጠርጣሪ ወደ ሰሜን አፍሪካዋ ሀገር አልጀሪያ ሌላኛው ደግሞ ወደ ምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ማሊ ለመብረር አቅደው ነበር ተብሏል፡፡
ትናንት ምሽት በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለት ግለሰቦች በሙዚየሙ የፈጸሙትን ስርቆት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማጣራት ፖሊስ ለተጨማሪ 96 ሰዓት ምርመራ ሊያደርግ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
ሙዚዬሙ ከቀናት በፊት ሌቦች በመሰላል በመውጣት መስታወት በመስበር በፈፀሙት ስርቆት 102 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የወርቅ ካባዎች፣ እንቁዎች እና ወርቆችን ተሰርቀውበታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።፡
የፈረንሳይ ፍትሕ ሚኒስቴር ደህንነት ካሜራዎች እና የአደጋ ጊዜ ደውሎች በጊዜያዊነት መዘጋታቸው ሌቦች ሰርቆቱን በቀላሉ እንዲፈፅሙ ማድረጉን ገልፆ፤ ለዚህም የፈረንሳይ ደህንነት ፕሮቶኮሎችን ወቅሷል፡፡
ከሙዚዬሙ ከተሰረቁ ጌጣጌጦች መካከል የናፖሊዮን 3ኛ ሚስት ንግስት ኢውጂን ጌጥ እንደሚገኝበት ተገልጿል፡፡
በማዕካለዊ ፓሪስ የሚገኘው የፈረንሳዩ ሎቭር ሙዚዬም የሊዮናርዶ ዳቬንቺ ድንቅ ፈጠራ የሆነው የሞናሊዛ ስዕልን ጨምሮ ከአንደኛው እና ሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተገኙ ውድ ጌጣጌጦች እና ታሪካዊ አልባሳት መገኛ ነው፡፡