በኦሮሚያ ክልል ከ2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል አሁን ላይ ሁለት ሚሊየን በላይ ተማሪዎች የት/ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል አለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፡፡
የቢሮው ም/ሃላፊ ቡልቶሳ ኢርኮ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በ2018 በጀት ዓመት በሁሉም የክፍል ደረጃ 12 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት፡፡
በዚህ መሰረትም የትምህርት ግብዓቶችን የሟሟላት ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በተለይም የመማሪያ መጽሐፍትን በሁሉም የክፍል ደረጃዎች በበቂ ሁኔታ ለማሰራጨት በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
የመምህራንን አቅም የማሳደጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ÷ ወላጆችም ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በክልሉ የተማሪዎች የት/ቤት ምገባ አገልግሎት የትምህርት ክትትልን ከማሳደግ ባለፈ የመቅረት ምጣኔን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት ም/ሃላፊው ÷ በዓመቱ 8 ሚሊየን ተማሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ