Fana: At a Speed of Life!

ታሪካዊ ስህተትን የሚያርመው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ …

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጸሙባትን ስህተቶች የሚያርም ነው አሉ ምሁራን።

ምሁራኑ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፤ የባሕር በር ጉዳይ የአሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፋንታ ይወስናል።

‎በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪው አብዱ መሐመድ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ያጣችበት አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነው ብለዋል።

በየዘመኑ የሉዓላዊነት ፈተናዎችን እየተጋፈጠች እዚህ የደረሰችው ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን ለመመለስ ትውልዱ በትጋት መስራት እንዳለበት ገልጸው፤ ጥያቄው ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል ነው ያሉት።

‎በመንግስት የተነሳው የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ያልተቋረጠ ጥረት መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በአጀንዳው ላይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ መስራት አለባቸው ብለዋል።

‎በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪው ሰይድ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ማህበረሰብ አባልነት እንድትወጣ የተደረገው ተገቢ ባልሆነ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ጫና ማስከተሉን አስታውሰው፤ አሁን ላይ የተነሳው የባህር በር ጥያቄ የፍትህ እና ርትዕ ጥያቄ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ጠንካራ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበው፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ ትግል ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

‎እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
‌‎
‎ በኢብራሂም ባዲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.