Fana: At a Speed of Life!

በአስተሳሰብም በድርጊትም ያቆሰልነውን ህዝብ መካስ አለብን – የስምረት ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት (ስምረት) ፓርቲ ምክር ቤት አባላት በአስተሳሰብም በድርጊትም ያቆሰልነውን ህዝብ መካስ አለብን አሉ።
ፓርቲው በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የስምረት ፓርቲ ምክር ቤት አባል ጠዓመ ዓረዶም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ፓርቲው ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን በመረዳት ለትግራይ ክልል ህዝብ የሚያስፈልገውን ለውጥ ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳው ነው።
የህወሃት አንደኛው ክንፍ የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን የተለያዩ ተግባሮችን በማድረጉ ፓርቲው ህጋዊ ሰውነቱን እንዲያጣ ሆኗል ሲሉም አንስተዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነትን የማይቀበሉ ኃይሎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ የፕሪቶሪያን ስምምነት ተቀብሎ በማስፈጸም የትግራይን ጥቅም ማስጠቅ እንደሚገባ ስምረት ፓርቲ እምነቱ እንደሆነ አመልክተዋል።
ፕሪቶሪያ ሄደው ስምምነቱን የፈረሙ አካላት ትግራይን ብሎም መላ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ነገር በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የስምረት ፓርቲ ምክር ቤት አባል ከላሊ አድሃና (ዶ/ር)፤ በአስተሳሰብም በድርጊትም ያቆሰልነውን ህዝብ መካስ አለብን ነው ያሉት።
የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ምንም ጥቅም የሌለው በመሆኑ ሰላማዊ መንገድን መከተል ብቸኛ መፍትሄ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከማህበረሰቡ ጋር በመመካከር እና ያለበትን ሁኔታ በሚገባ በመገንዘብ መፍትሄ መስጠት አለብን ብለዋል።
የትግራይ ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ፓርቲያችን ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።
ስምረት ፓርቲ ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ባደረገው መስራች ጉባኤ አቶ ጌታቸው ረዳን ፕሬዚዳንት አድርጎ መምረጡ ይታወሳል።
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.