Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው – የዓለም ባንክ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ለመጣው የኢኮኖሚ እድገት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው አሉ በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማሪያም ሳሊም፡፡

ማሪያም ሳሊም ዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር መሆኑን ገልጸው ÷ በተለያዩ ዘርፎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለአብነትም በግብርና፣ ሎጂስቲክስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ሥራ እድል ፈጠራና በሌሎች ዘርፎች በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያስመዘገበችው ውጤት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለዚህም የማክሮ ኦኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል ያሉት ዳይሬክተሯ÷ ይህም የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ዘላቂና አካታች ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

በተለይም በማኑፋክቸሪንግ እና አገልግሎት ዘርፍ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ ምርታማነት ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ልማትን ከግብ ለማድረስና ኢኮኖሚን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመው÷ ለሥራ እድል ፈጠራ መስፋፋት ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ማሪያም ሳሊም የዓለም ባንክ በተለያዩ ዘርፎች ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.