Fana: At a Speed of Life!

የባሕር በር ጥያቄው የሕዝብን ፍላጎትና ጥቅም ማዕከል ያደረገ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሕዝቡን ፍላጎትና ጥቅም ማዕከል ያደረገ ነው አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡

አቶ አደም ፋራህ ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ÷ በሁሉም ዘርፎች ያሉ እምቅ አቅሞችን በመጠቀም ልማት ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የወጣቶችን ተስፋ የሚያለመልሙ እና የሚያበረታቱ ሥራዎች ላይ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ለአብነትም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የወጣቱን ፍላጎት እና ጥቅም ማዕከል በማድረግ የዛሬ እና የነገ ትውልድን መጻኢ እድል ለማሳመር ታስቦ የተቀረጸ ነው ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማትም የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር እና የቱሪስት መዳረሻነትን ከማስፋት ባሻገር ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታን ለማስፋት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ወጣቱ አዳዲስ የፈጠራ ችሎታ እንዲኖረው በማነሳሳት ለሥራ እድል ፈጠራ በር የከፈተ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር ሊኖራት ይገባል የሚለው ጥያቄም የሕዝቡን በዋናነት የወጣቱን ፍላጎት እና ጥቅም ማዕከል በማድረግ የተነሳ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት መንገድ ኢፍትሃዊ መሆኑን ጠቁመው ÷ አሁን ላይ በጉዳዩ ዙሪያ የተፈጠረው ግንዛቤ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የባሕር በር ጥያቄው ስኬታማ እንዲሆንም ወጣቱ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ነው አቶ አደም ፋራህ ያስገነዘቡት፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.