የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም በፓሪስ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በፎረሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን የአፍሪካ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጌዛ ስትራመር እና የፈረንሳይ የወጪ ንግድ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር መልዕክተኛ ኒኮላስ ፎርሲየር ተሳትፈዋል፡፡
መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከርና አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
አቶ አሕመድ ሺዴ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ሪፎርሙ የግል ኢንቨስመንትን መሳብ እና ኢትዮጵያ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያላትን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በፎረሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉ ባለስልጣናትም የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ ትብብር እያደገ መምጣቱን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል እያከናወነቻቸው ያሉ ሥራዎችንም አድንቀዋል።
የኢንቨስትመንት ምቹነትን ለማሻሻልና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እያደረገቻቸው ያሉ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ምክክሮች መልካም የሚባሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በግብርና ንግድ፣ የታዳሽ ኃይል፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና መሰረተ ልማትን ጨምሮ ቁልፍ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድሎች ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም በኢትዮጵያ ተቋማትና በአውሮፓ ኩባንያዎች መካከል በኢኖቬሽን፣ በእሴት መጨመርና የጋራ ብልጽግናን መደገፍ ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጎልበት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡