በመዲናዋ የምግብና የፍጆታ ምርቶች በኅብረት ስራ ማህበራት በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመዲናዋ የምግብና የፍጆታ ምርቶች በ154 መሰረታዊ የኅብረት ስራ ማህበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው አለ የአዲስ አበባ ኅብረት ስራ ኮሚሽን።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሃብተየስ ዲሮ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፥ በኅብረት ሥራ ማህበራት በሰንበት ገበያ፣ በሸማች ሱቆች እንዲሁም በህዝብ መዝናኛ ቦታዎች ምርቶችን በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋት ስራ እየተሰራ ይገኛል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት ሻጭና ሸማቾች የሚገናኙበት ትስስር በመፈጠሩ አበረታች ውጤቶች ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
የሚቀርቡ ምርቶች ዋጋ ተመጣጣኝና የነዋሪውን ፍላጎት ያማከለ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፥ በተለይም በግብርና ምርቶች አቅርቦት ላይ ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የዘርፉ ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ያለ አግባብ ግለሰቦች ሲጠቀሙባቸው ከነበሩ 2 ሺህ 885 ቦታዎች ውስጥ ከ1 ሺህ 250 በላይ የሚሆኑትን በማስለቀቅ ሸማቾች እንዲሰሩበት ተደርጓል ብለዋል፡፡
የማህበራቱ የጥራት ኮሚቴ አረጋግጦ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያስገባበት አሰራር መኖሩንና በሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ለአቻ ማህበራት ተሞክሮ የሚሆን ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በምርቶቹ ላይ የጥራት ጉድለት ካለ ተመላሽ እንደሚደረግ ገልጸው፥ ህብረተሰቡ የምርት ጥራት ጉድለት ሲያጋጥመው ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት