Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በመካከለኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የፈረንሳይ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (ኢ ዲ ኤፍ) አመራሮች ተፈራርመዋል፡፡

የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ ከሚገኘው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም ጎን ለጎን ነው የተካሄደው፡፡

በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ ተቋማት በመካከለኛ መስመር ዝርጋታ እና ኃይል ሳይቋረጥ የኤሌክትሪክ መስመሮችን መጠገን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በትብብር የሚሰሩ ይሆናል፡፡

በተጨማሪም በቴክኒክና ሥልጠና ድጋፍ፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በአቅም ግንባታ እና የብድር ስምምነትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) ÷ ስምምነቱ የተቋሙን የቴክኒክ አቅም በማጠናከር ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የኔትወርክ ጥገና ለማከናወን ያስችላል ብለዋል፡፡

ይህም የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ይበልጥ በማጠናከር የኃይል ዘርፉን ለማዘመን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ነው ያስረዱት፡፡

በሌላ በኩል አገልግሎቱ ቴምስ ኤሌክትሪካል ከተሰኘ የኬንያ ድርጅት ጋር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓቶችን በኢትዮጵያ ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል፡፡

በዚህም ቴምስ ኤሌክትሪካል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓቶችን በኢትዮጵያ ለማምረት ፍላጎት እንዳለው መግለጹን የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.